በህንድ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የኢንቨስትመንት፣ ንግድና ቱሪዝም ማስተዋወቂያ መድረክ አካሂደ

80

ጥር 22/2013 (ኢዜአ) በህንድ ኒውዴልሂ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ “Confederation of Indian Industry (CII)” ከተባለ የህንድ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ም/ቤት ጋር በመተባበር የኢ.ፌ.ዲ.ሪ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በተገኙበት ከ130 በላይ የህንድ ኩባንያዎች የተሳተፉበት የቨርችዋል የማስተዋወቂያ መድረክ ትላንት ተካሂዷል።

በመድረኩ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ፣ በህንድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ትዝታ ሙሉጌታ፣ በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግን ጨምሮ የቱሪዝም ኢትዮጵያ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዲሁም የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የስራ ኃላፊዎች ተገኝተው ገለፃ አድርገዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ አረጋ በመድረኩ መክፈቻ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያና ህንድ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ታሪካዊ ትስስር ያላቸው ሀገሮች መሆናቸውን ገልጸው፤ የውጭ ንግድንና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት የኢትዮጵያ መንግስት እየወሰዳቸው ያሉ ኢኮኖሚያዊ ሪፎርሞችን አስመልክቶ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የውጭ ንግድ ለማሳደግ፣ የሚያጋጥሙ የንግድ ማነቆዎችን ለመቀነስ እና መልካም የንግድ ግንኙነት ለመገንባት የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ በመግለጽ፤ በኢትዮጵያ ካለው ምቹ የኢንቨስትመንት እድል አንፃር የህንድ ባለሃብቶች ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

በህንድ የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ዶ/ር ትዝታ ሙሉጌታ እንዳሉት በኢትዮጵያ ያለው የተረጋጋ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስርዓት፣ የተማረና አምራች የሰው ሃይል፣ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት፣ ሰፊ ገበያ መኖሩን ገልጸዋል።

በተጨማሪም መንግስት ለዘርፉ የሰጠው ከፍተኛ ትኩረትና የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎችን በመጠቀም የህንድ ባለሃብቶች በሀገሪቱ ኢንቨስት ቢያደርጉ ተጠቃሚ ይሆናሉ ብለዋል።

ከኢትዮጵያ ወደ ህንድ የሚገቡ ምርቶችን በጥራትና በመጠን ለመጨመር በቀጣይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ የገለፁት አምባሳደሯ፤ የህንድ ባላሃብቶች ካላቸው የቴክኖሎጂና ከፍተኛ ልምድ አንጻር እሴት በሚጨምሩ ዘርፎች፣ በአግሮ-ፕሮሰሲንግ፣ በማኑፋክቸሪንግና በቱሪዝም ዘርፎች መዋለ-ንዋያቸውን እንዲያፈሱም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የህንድ አምባሳደር ሮበርት ሼትኪንቶንግ በበኩላቸው በኢትዮጵያ በነበራቸው አጭር ቆይታ መንግስት የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ከፍተኛ ትኩረት መስጠቱን እንደተገነዘቡ ገልፀው፤ የህንድ ባለሃብቶች ሊሳተፉ የሚችሉባቸው ብዙ ዘርፎች መኖራቸውንም ነው ያስታወቁት።

በኢትዮጵያ ኢንቨስት ያደረጉ ሶስት የህንድ ኩባንያዎች ልምዳቸውን ለተሳታፊዎች ያካፈሉ ሲሆን፤ ከተሳታፊዎች ለተነሱ ጥያቄዎችም ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም