አቶ ደመቀ መኮንን የአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር አካላት በተገኙበት መድረክ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ማብራሪያ ሰጡ

113

ጥር 22/2013 ( ኢዜአ) ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በአትላቲክ አውስል የተሰኘ የአሜሪካ ቲንክ-ታንክ ተቋም ባዘጋጀው የበይነ መረብ መድረክ ላይ በመሳተፍ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ለተሳታፊዎች ገለፃ ሰጥተዋል።

በውይይቱ ላይ የአሜሪካ የኮንግረስ አባላት እና የአዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር አካላት ተሳትፎ አድርገዋል።

ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋሁን ጎበሳይ በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን ለተሳታፊዎች ያደረጉት ገለፃ በትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ፣ በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ የሚደረግ ርብርብ፣ የመልሶ ማቋቋም፣ የህወሃት ቡድን ያፈራረሳቸው የመሰረተ ልማቶችን መልስ ግንባታ፣በክልሉ እንቅስቃሴ ከማድረግ ጋር የሚነሳ ጥያቄ እና በክልሉ የሰብአዊ መብት ጥበቃ በተመለከተ የሚነሱ ክሶች፣ በትግራይ ክልል ባሉ የመጠሊያ ጣቢያዎች የሚገኙ የኤርትራ ስደተኞች ሁኔታ፤ እንዲሁም በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ላይ ያተኮረ ነበር።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በገለፃቸው የህወሃት ቡድን በትግራይ ክልል ባለው የአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ አስነዋሪ ጥቃት በመፈፀም የተገባበት የህግ ማስከበር ዘመቻ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዘመቻውንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ገልፀው፣ ከኦፕሬሽኑ በኋላ በክልሉ መረጋጋት ለማስፈን፣ ዘመቻው ከመካሄዱ በፊት በሴፊትኔት የድጋፍ ማዕቀፍ የሚረዱ 1.8 ሚሊዮን ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ የማድረስ፤ እንዲሁም በተፈጠረው ሁኔታ የሰብአዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ተጨማሪ ሰባት መቶ ሺ ሰዎች ሰብአዊ ድጋፍ እንዲደርስ ለማድረግ በተሰራ ሥራ ለ1 ሚሊዮን 46ሺ ሰዎች የሰብአዊ እርዳታ ማድረስ መቻሉን ገልጸዋል።

እንዲሁም በአንዳንድ አካላት ሪፖርት የሚቀርብና በክልሉ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ ፈላጊዎች 4.6 ሚሊዮን ተብሎ የሚቀርበው በተጨባጭ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ መሆኑንም ገልፀዋል።

አቶ ደመቀ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ስለሁኔታው መገንዘብ ያለበትን እውነታን አጽኖት በመስጠት አስረድተዋል።

በዋናነት የህወሃት ቡድን በአገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ እና በማይካድራ የፈፀመው ኢሰብአዊ ድርጊት፣ በመሰረተ ልማቶች ላይ ያደረሰው ውድመት የሰብአዊ ድጋፎች ለማድረስ የፈጠረው ጫና፣ በመሰረተ ልማት አውታሮች ላይ ጁንታው የፈፀመው የማፍረስ እርምጃ የተለያዩ አገልግሎቶች ላይ መቋረጥ አስከትሏል ብለዋል።

በዜጎች ላይ የተፈጠረው አስቸጋሪ ሁኔታን በአጠቃላይ በክልሉ የፈጠረው ውስብስብ ችግር የህወሃት ቡድን ሆነ ብሎ የፈጠረውና ከዚያ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በመፈለጉ ነው ብለዋል።

ቡድኑ በአጠረ ጊዜ ተሸንፎ ለህግ ተጠያቂነት በመቅረብ ላይ መሆኑንም ገልፀዋል።

ከኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ አንፃር ያለውን እና ኢትዮጵያ ጉዳዩን ለመፍታት ያላት አቋም በግልፅ የተቀመጠ መሆኑንም አስረድተዋል።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገር ሱዳን ጋር ወደ አላስፈላጊ ግጭት መግባት እንደማትፈልግ፣ ለዚህም ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድና በድርድር እንዲፈታ ቁርጠኛ ናት ነው ያሉት።

ጉዳዮ ሁለቱም አገራት በጋራ ባቋቋሙት እና ሲሰራበት በቆየው የመፍትሄ ሂደት መሰረት ሊፈታ እንደሚችል ኢትዮጵያ እንደምታምን፣ የድንበር ጉዳዩን ለመፍታት ወደ ድርድር ጠረጴዛ ለመመለስ ሱዳኖች በቅርብ ጊዜ ድንበር ጥሳ ገብታ ከያዘቻቸው ቦታዎች ሙሉ በሙሉ ለቃ መውጣት በቅድመ ሁኔታነት መቀመጡም ተገልጿል።

ምንጭ-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም