ክልሉ ከችግር በመውጣት በልማትና መልካም አስተዳደር አመርቂ ወጤት እያስመዘገበ ነው-አቶ አገኘሁ ተሻገር

100

ባህር ዳር ጥር 21/2013 (ኢዜአ) የአማራ ክልል ባለፉት ጊዜያት ከገጠሙት ውስብስብ ችግሮች በመወጣት በልማትና መልካም አስተዳደር አመርቂ ወጤት እያስመዘገበ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አስታወቁ።

ለቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ትላንት አሸኛኘት ተደርጎላቸዋል ።

በባህር ዳር ከተማ በተዘጋጀው የሽኝት ስነ-ስርአት  ላይ የክልል ርዕሰ መሰተዳደሮች ተገኝተዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በወቅቱ እንደገለጹት ክልሉ ባለፉት ጊዜያት ውስብስብ ችግሮች አጋጥመውት ነበር ።

በተለይም በ2011 ዓም የተፈጠረን ክስተት ተከትሎ ክልሉ በሁለንተናዊ መንገድ ችግር ውስጥ መውደቁንና መስዋትነት ጭምር መከፈሉን አስታውሰዋል።

ክልሉን ከገጠመው አስቸጋሪ ሁኔታ ለማውጣት ከፍተኛ ጥረት መደረጉን አስታውሰው በተከፈለ መስዕዋትነትና ቁርጠኛ አመራር በአጭር ጊዜ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት መቻሉን አመልክተዋል።

"አሁን ላይ በክልሉ የተረጋጋ ስላም ተፈጥሯል" ያሉት ርዕሰ መሰተዳድሩ  በክልሉ ህዝቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የልማትና መልካም አስተዳደር ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የቀድሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ጥበብና ወኔ የተሞላበት አመራር መስጠታቸው ክልሉ የገጠሙትን ፈተናዎች ለማለፍ እንዲበቃ ትልቅ አስተዋጾ ማድረጉን ጠቁመዋል"

የተገኙ ለውጦችን የበለጠ ለማስቀጠልና ብልፅግናን ለማረጋገጥ አሁን ያለው አመራር ካፈው ልምድ በመቅሰም ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን  ርዕሰ መስተዳደሩ አስታውቀዋል።

"አመራርነት የሚለካው በችግርና በጭንቅ ወቅት ነው" ያሉት ደግሞ የቀድሞው የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርና የአሁኑ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ናቸው።

"በዚያን ወቅት የገጠመው ፈተና ለክልሉም ሆነ ለሃገሪቱ ሰላምና ደህንነት ስጋት የፈጠረ ነበር" ሲሉም አስታውሰዋል።

ክልሉን ከችግር ለማውጣት ጠንከራ አመራር በመስጠትና መልሶ በማደራጀት ለሰላምና መረጋጋት፣ ለልማት፣ ለመልካም አስተዳደርና ለኢኮኖሚያዊ  ስራዎች ትኩረት ተሰጥቶ መሰራቱን አመልክተዋል።

ባለሃብቶችን ከውጭ ጭምር በማስመጣት የኢንቨስትመነት ዘርፉ እንዲነቃቃ ከማድረግ ጀምሮ በየዘርፉ በተሰሩ ስራዎች በአጭር ጊዜ ሊታይ የሚችል ለውጥ ማምጣት መቻሉን ጠቅሰዋል።

"የሃገሪቱም ሆነ የክልሉ ሰላም እንዲናጋ በውጭ የሚኖሩ ግጭት ጠማቂዎችና በሃገር ውስጥ ያሉ ግጭት ፈጣሪዎች ዋናዎቹ ስግብግቡ ጁንታ ነበሩ" ብለዋል።

ጁንታው ሃገሪቱንም ሆነ ክልሉን ለማፍረስ በሞከረው ትንኮሳ እስከነ አካቴው ተደምሰሶ ታሪካዊ ጠባሳ ጥሎ ማለፉን ተናግረዋል።

ጁንታው የፈጠራቸው የመጠፋፋት፣ የመከፋፈል፣ የዘረኝነት፣ የሌብነትና የማታለል ስራዎችን ለማጥፋት የተጀመሩ ስራዎችን  ማጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ጠናክራ ሃገር እንድትሆን ህዝብን መሰረት በማድረግ ተባብሮ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል።

በስራ ወቅት በነበሩበት ጊዜ የላቀ ድጋፍና ትብብር ሲያደርጉላቸው ለነበሩ ሁሉ አቶ ተመስገን ምስጋና አቅርበዋል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በበኩላቸው "አሁን ላይ ሀገሪቱ  ብዝሃነትን ተቀብሎ የሚያስተናግድ መሪ ያስፈልጋታል" ብለዋል ።

አቶ አደም በማያያዝ "አቶ ተመስገን ጥሩነህ ፅንፈኝነትን አብዝተው የሚጠሉና በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ በሳል አመራር ናቸው" ብለዋል።

"ክልሉ ችግር ውስጥ በወደቀበት ወቅት የመሪነት ጥበባቸውን ተጠቅመው አሁን ላለበት ሁኔታ በማድረሳቸው የተሰጣቸው እውቅና ለሌሎች ትምህርት የሚሆን ነው " ሲሉም አድናቆታቸውን ችረዋል።

''አቶ ተመስገን በችግር ወቅት ለአማራና ለኢትዮጵያ ህዝብ የደረሱ የቁርጥ ቀን መሪ ናቸው'' ያሉት ደግሞ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዴሳ ናቸው።

"አቶ ተመስገን ለኢትዮጵያ አንድነት ሳይሰስቱ የሚሰሩና በችግር ወቅት ሆነው ከችግር ማዶ ያለውን እድል የሚያሳዩ ጥበበኛ መሪ ናቸው " ሲሉም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

"ሁላችንም ከህዝብ ዘንድ የሚቀር ስራ መስራት ይገባናል፤ የምንፈልጋትን ሃገር ለመገንባት በጋራ መስራት ወቅቱ የግድ ይለናል" ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።

በሽኝት ስነ-ስርአቱ ላይ የትግራይ ጊዜያዊ ስራ አስፈፃሚ፣ ጨምሮ የአፋር፣ የደቡብ፣ የጋምቤላ፣ የሱማሌ ርዕስ መስተዳደሮችም መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን ለአቶ ተመስገን ጥሩነህ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም