በኢሉአባቦር ዞን ከ1ሺህ 500 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት እየተሰራ ነው

78

መቱ፤ ጥር 21/2013 (ኢዜአ) በኢሉአባቦር ዞን ለመጀመሪያ ጊዜ ከ1ሺህ 500 ሄክታር በሚበልጥ መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ለስንዴ ልማቱ ያለውን አመቺነት በመጠቀም አርሶ አደሩ በንቃት እንዲሳተፍ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ተመልክቷል።

በመጀመርያው ዙር በአራት ወረዳዎች 160 ሄክታር መሬት ስንዴ በመስኖ መልማቱነ የጽህፈት ቤቱ ምክትል ሀላፊ አቶ ሺፋ ጣሂር ለኢዜአ ተናግረዋል።

በሁለተኛው ዙር ደግሞ  ልማቱን ወደ 1500 ሄክታር ለማሳደግ  የማሳ ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በበቾ ወረዳ  ያሚ ቀበሌ አርሶ አደር ጌታሁን ጎበና በሰጡት አስተያየት ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በግብርና ባለሙያዎች እየታገዙ ስንዴን በመስኖ ማልማት መጀመራቸውንና እስካሁን  የሰብሉ ቁመና በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

"ልማቱ ተስፋ ሰጪ ቢሆንም የውሀ መሳቢያ ሞተር እጥረት አለብን" ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ስንዴን በመስኖ  እያለሙ ያሉት ሁለት ጥማድ ማሳ በሁለተኛው ዙር መስኖ አሰፋፍተው ለማሳደግ ማሳቸውን ማዘጋጀታቸውን የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር ረጋሳ ጆቴ ናቸው።

የበቾ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ኢብራሂም ጉደታ እንዳሉት በወረዳው በመስኖ እየለማ ካለው 414 ሄክታር መሬት ውስጥ 20 ሄክታር የሚሆነው በስንዴ የተሸፈነ ነው።

ስንዴን በመስኖ የማልማት ስራ በአካባቢው አዲስ እንደመሆኑ አርሶአደሮች የውሀ መሳቢያና የሌላም ግብአት  እጥረት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

ችግሩን  በመፍታት ልማቱን ለማስፋፋት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

በኢሉአባቦር በዘንድሮው የመጀመርያ ዙር መስኖ ከ5ሺህ 256 ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ፣ በቆሎ እና የተለያዩ የጓሮ አትክልቶች እየለማ እንደሚገኝ የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አመልክቷል።

ከልማቱም ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል።

በኦሮሚያ ክልል ደረጃ  ከውጭ የሚገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ለመተካት በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ከ300 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ላይ ስንዴን በመስኖ ለማልማት እየተሰራ መሆኑን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ቀደም ብሎ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም