በህብረተሰቡና በባለድርሻዎች የተቀናጀ ጥረት በተከናወኑ የሰላምና የልማት ስራዎች ውጤት ተገኝቷል- አስተዳደሩ

57

ሐረር ጥር 20 /2013 (ኢዜአ)  ባለፉት ስድስት ወራት በህበረተሰቡና በባለድርሻዎች የተቀናጀ ጥረት በተከናወኑ የሰላም ፣ የልማትና የህግ ማስከበር ስራዎች አበረታች ውጤት መገኘቱን የምስራቅ ሐረርጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ በስድስት ወራት በተከናወኑ የሰላም፣ የልማትና የህግ ማስከበር  ስራዎች ላይ  ግምገማ  እየተካሄደ ነው ።

የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሁሴን ፈይሶ በወቅቱ እንደገለጹት በዞኑ ባለፉት ዓመታት የነበረ የጸጥታ ችግር  ለህብረተሰቡ ሰላምና ልማት ተግዳሮት ሆኖ ቆይቷል።

በተያዘው በጀት ዓመት በመንግስት፣ በጸጥታ ሀይሉና በህብረሰተቡ የነቃና የተቀናጀ ተሳትፎ በተከናወኑ የሰላም፣ የልማትና የህግ ማስከበር   ስራዎች  አበረታች  ውጤት  መገኘቱን ተናግረዋል ።

በዞኑ በተለይም በኦነግ ሸኔና በጁንታው የህወሀት ቡድን  ሴራ ብሔርና ሃይማኖትን ሰበብ በማድረግ ይከሰቱ የነበሩ የጸጥታ ችግሮች በዚህ አመት ተወግደው አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በዞኑ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ስራዎችም በተያዘላቸው የጊዜ  ሂደት እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በዞኑ ባለፉት ስድስት ወራት ህብረተሰቡ ባደረገው 365 ሚሊየን ብር ግምት ያለው የገንዘብ፣ የቁሳቁስና የጉልበት ድጋፍ 3 ሺህ 76 የመማርያ ክፍሎች ተገንበተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል ።

በግብርና ዘርፍ በአርብቶ አደር ወረዳዎች ከ69 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት  ላይ  እየተከናወነ  ያለውን የመስኖ ልማትም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

የመንገድ ግንባታና ሌሎች የተጓተቱ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም ላይ የታየን ክፍተት በአንጻራዊነት የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው የአንበጣ መንጋ ክስተት በግብርና ስራ ላይ እያደረሰ ያለውን አሉታዊ ተጽእኖ እንደ ችግር አንስተዋል ።

በዞኑ ያልተፈቱና እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በቀጣይ  ስድስት  ወራት  በትኩረት  እንደሚሰራ ዋና አስተዳዳሪው አስታውቀዋል ።

"በዞኑ በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ፣ በልማትና በጸጥታ በኩል ደካማና  ጠንካራ ጎኖችን  በመለየት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማጎልበት ወደ  ስራ በመገባቱ አመርቂ ውጤት  ተመዝግቧል" ያሉት ደግሞ  የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመዲን ኡስማኤል ናቸው።

"የህዝብ አደረጃጀቶችን በማጠናከርና በማጎልበት ህብረተሰቡ በፖለቲካ በኢኮኖሚዊና  በማህበራዊ መስኮች ተጠቀሚ እንዲሆን   ጥረት ተደርጓል" ብለዋል።

የዞኑ የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ጽሀፈት ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ናጂ አቡበከር  በበኩላቸው  በዞኑ የሚገኙ የጸጥታ አካላትን  ወስጣዊ ችግሮች በመፍታትና  የአቅም  ግንባታ ስልጠና በመስጠት ሰላምን ለማረጋገጥ  የሚያችሉ ተግባራት መከናወናቸውን አመልክተዋል።

የጸጥታ አካላትና ህብረተሰቡ በጋራ ባከናወኑት እንቅስቃሴ 700 የሚደርሱ የተለያዩ ህገ  ወጥ ጦር መሳሪያዎችና በኦነግ ሸኔ ጋር ግንኙነት ያላቸው 598 ሰዎች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን ጠቅሰዋል ።

እንደ ሀላፊው ገለጻ በቁጥጥር ስር ለዋሉ ለቡድኑ አባት የተሃድሶ ስልጠና የተሰጠ  ሲሆን ለህግ መቅረብ ያለባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እንዲታይ  ተደርጓል።

ሶስት ቀናት በሚካሄደው የግምገማ መድረክ ከ1ሺህ 500 በላይ የዞንና የወረዳ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም