በአማራ ክልል በመጭው ክረምት የሚተከል 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ እየተዘጋጀ ነው

202

ባህርዳር፤ ጥር 21/2013 (ኢዜአ) በአማራ ክልል በመጭው ክረምት በአረንጓዴ አሻራና በመደበኛው መርሀ ግብር የሚተከል 1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ እስመላለም ምህረት ለኢዜአ  እንደገለጹት ችግኙ እየተዘጋጀ ያለው በመንግስት፣ በግልና በማህበር በተቋቋሙ ከ96 ሺህ  በላይ የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች ነው።

እንደየአካባቢው ስነምህዳር ተስማሚ የሆኑ ችግኞችን በመለየት የዝግጅት ስራው  እየተከናወነ መሆኑንም ተናግረዋል።

ችግኞቹ ለደን ልማት፣ ለእንሳሰት መኖ፣ ለፍራፍሬ ምግብነትና ለሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ የሚውሉ የዛፍ ዝርያ አይነቶች መሆናቸውን በማመልከት፤ እስካሁን 68 ሚሊዮኑ ለተከላ በሚያበቃቸው ደረጃ ላይ ናቸው ነው ያሉት።  

እየተዘጋጁ ካሉት መካከል ዋንዛ፣ ወይራ፣ ኮሶና ዝግባ ሀገርበቀል የዛፍ ዝርያዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰው፤

ችግኞቹ 182 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍኑ  መሆናቸውን የገለጹት አቶ እስመላለም፤  ባለፉት አመታት በተተከሉ ችግኞች የክልሉ የደን ሽፋን 14 ነጥብ 6 በመቶ መድረሱን  አስታውቀዋል።

"የደንን ጠቀሜታ በአግባቡ እየተረዳን በመምጣታችን በግልና በወል መሬት በየዓመቱ  የምንተክላቸውን ችግኞች በመንከባከብ እያሳሳደግን እንገኛለን " ያሉት ደግሞ በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ የኮለል ለቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶአደር ስሜነህ ሞላልኝ ናቸው።

በመጭው ክረምት የሚተከል 10 ሺህ ችግኝ እያዘጋጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።  

ከዚህ ቀደም ከተከሏቸው የዛፍ ችግኞች ሽያጭ  300 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን አርሶ አደሩ አስታውቀዋል።

በክረምት ወቅት የሚተከሉ 2ሺህ የዋንዛ፣ዶቅማ፣ግራቢሊያና ብሳና ችግኞች እያዘጋጁ   መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ  በባህርዳር ዙሪያ ወረዳ የጎምባት ቀበሌ ነዋሪ  አርሶ አደር አዲሱ መንግስቴ ናቸው።

በክልሉ ባለፈው  ክረምት በመደበኛውና  በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር  ከተተከሉ  1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ችግኝኞች  87 በመቶ መፅደቁን የክልሉ ግብርና ቢሮ መረጃ  ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም