በመስኖ ልማት ከ134 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በስንዴ ተሸፍኗል - ግብርና ሚኒስቴር

70

አዲስ አበባ፣ ጥር 20 ቀን 2013 (ኢዜአ) በተያዘው ዓመት በመስኖ ለማልማት ከታቀደው በመጀመሪያው ዙር ከ134 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ስንዴ መልማቱን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ።

በሁለት ዙር 214 ሺህ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት መታቀዱንም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ የግብርና ኤክስቴንሽን ዳይሬክተር አቶ ገርማሜ ጋሩማ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በኢትዮጵያ በየዓመቱ ከ45 እስከ 50 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ቢመረትም አገራዊ ፍጆታው ከ60 እስከ 65 ሚሊዮን ኩንታል ነው።

በመሆኑም መንግስት በየዓመቱ ከ15 እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል ስንዴ ከውጭ ለማስገባት ተገዷል፡፡

መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት ይህን ክፍተት ለመሙላትና የስንዴ ፍላጎቱን በአገር ውስጥ ምርት ለመሸፈን እየሰራ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።

በመጀመሪያው ዙር የመስኖ ልማት ቅድመ ዝግጅቶች መደረጋቸውን የገለጹት አቶ ገርማሜ፤ ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ መሰራጨቱንና ዘርና ኬሚካል እየቀረበ እንደሆነም አብራርተዋል።

"የባለሙያዎችና የአርሶ አደሮች ስልጠና በመተግበሩ የተያዘውን ዕቅድ ማሳካት ይቻላል" ብለዋል።

የመስኖ ስንዴ ልማቱን ስኬት እውን ለማድረግ ባለፉት ሶስት ዓመታት በሱማሌ፣ በደቡብ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በአማራና በጋምቤላ ክልሎች እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት በ20 ሺህ ሄክታር መሬት ስንዴ በመስኖ ማልማት መቻሉን አስታውሰው፤ በዚህም በሄክታር ከ30 እስከ 40 ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል።

ቀድሞ አትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ይተዳደሩ እንደነበር የሚገልጹት የምዕራብ አርሲ ዞን የሂበንና የአዳባ ወረዳ አርሶ አደሮች ለስንዴ ማምረት አዲስ ቢሆኑም በመስኖ ልማቱ ጥሩ ምርት ለማግኘት ተስፋ ሰንቀዋል።

አርሶ አደሮቹ ከግብርና ባለሙያዎች የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ በማድረጋቸው ከስንዴ ማሳው በክረምት ያገኙ ከነበረው የበለጠ ምርት እንደሚያገኙ ተናግረዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም