የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማጠናከር የሚያስችል የአቅም ግንባታ ፕሮጀክት በ20 ከተሞች እየተካሄደ ነው

249
አዲስ አበባ ሃምሌ 17/2010 በኢትዮጵያ የተለያዩ 20 ከተሞች የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማጠናከር በተቀረፁ የአቅም ግንባታ ፕሮጀክቶች ትግበራ ለውጥ ያመጡ ከተሞችን ልምድ ለማስፋት እንቀስቃሴ መጀመሩ ተገለፀ። ከእነዚህ ከተሞች መካከል በአብዛኛዎቹ የሚገኙት የመጠጥ ውሃ አገልግሎት መስጫ ተቋማት አሰራር ኋላቀር በመሆኑ የሚፈለግባቸውን አገልግሎት በብቃት እየሰጡ አይደለም። 'ወተር ኤይድ' በተሰኘ ዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅት ድጋፍ የተቀረፀው ፕሮጀክት የውሃ ብክለትንና ብክነትን መቀነስን ጨምሮ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት አገልግሎት ላይ የሚታዩትን የአቅም ክፍተቶች ማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው። ከእንግሊዙ 'ዮርክሻየር ወተር' በተገኘ አንድ ሚሊዮን ፓውንድ ድጋፍ ተግባራዊ የሆነው ፕሮጀክቱ ያለፉት አራት ዓመታት ትግበራ ላይ የመከረ ውይይት  ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሂዷል። የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴርና ሌሎች የዘርፉ ተቋማት በተገኙበት በዚሁ መድረክ ላይ በፕሮጀክቱ ትግበራ ወቅት የተገኙ ለውጦች ይፋ ተደርገዋል። ከዚህም በተጨማሪ ፕሮጀክቱ ተግባራዊ ከሆነባቸው አራት ክልሎች የተመረጡ ሞዴል ከተሞች ልምድ ለመድረኩ ቀርቧል። በዚሁ ወቅት የወተር ኤይድ ኢትዮጵያ የቴክኒካል አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ማናየ ስዩም እንደተናገሩት፤ በአገሪቱ ያሉ የውሃ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባህላዊ አሰራርን የሚከተሉ በመሆናቸው የሚፈለገውን አገልግሎት እየሰጡ ባለመሆኑ ህብረተሰቡ ለእንግልት እየተዳረገ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የውሃ አገልግሎት ሰጪ ተቋማቱ ኃብታቸውን በወጉ የማስተዳደር ችግር እንዳለባቸውም አቶ ማናየ ገልፀዋል። የውሃ ተቋማቱ ላይ የሚስተዋሉትን ችግሮች ለመፍታት የውስጥ አቅምን ማሳደግ አስፈላጊ በመሆኑ እስካሁን በተከናወኑት የአቅም ግንባታ ስራዎች ሞዴል ሆነው የወጡ ከተሞች መኖራቸውን አብራርተዋል። የተቋማቱን የአገልግሎት አቅም ለማጠናከር ታስቦ የተቀረፀው ፕሮጀክት ትግበራን ተከትሎ በአንዳንዶቹ ከተሞች መሻሻሎች እየታዩ መሆናቸውን አመልክተዋል። ''በአንዳንድ ከተሞች በሚገኙ ተቋማት በታየው የንብረት አስተዳደር መሻሻል ሳቢያ በአንድ ከተማ ብቻ 20 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ያገለገሉ እቃዎችን በሽያጭ በማስወገድ ገቢ ማግኘት ተችሏል'' ብለዋል። የመድረኩ ዓላማ ከፕሮጀክቱ ተግበራ የተገኙ ልምዶችን የበለጠ በማሳደግ ወደሌሎች ከተሞች ማስፋት በሚቻልበት መንገድ ላይ መምከር መሆኑንም ጠቅሰዋል። በመሆኑም ፕሮጀክቱ በሞዴል ከተሞች እየተመራና በዙሪያቸው ካሉ ከተሞች ጋር በማጣመር ለመተግበር እንቀስቃሴ መጀመሩን ጠቅሰዋል። ወተር ኤይድ ፕሮጀክቱን በሌሎች የአገሪቱ ከተሞች እንዲተገበር ለማድረግ ከኢትዮጵያ ውሃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ካሉ የውሃ አገልግሎት ፎረምና ፌዴሬሽኖች ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ ነው ተብሏል። በመድረኩ ላይ የተገኙት የውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደተናገሩት፤ ወተር ኤይድ ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት አስርት አመታት በገጠርና ከተማ የመጠጥ ውሃ አቅርቦትን ለማሻሻል የሚደረገውን ጥረት ሲደግፍ ቆይቷል። ድርጅቱ ከንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት በተጨማሪ በዘርፉ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የስልጠናና የቁሳቁስ ድጋፎችን እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል። በ20 ከተሞች የተገኘውን ልምድ በመቀመር ወደሌሎች ከተሞች ለማስፋት ባለድርሻ አካላት በትኩረት ሊሰሩ እንደሚገባ ሚኒስትር ዲኤታው አሳስበዋል። በዚህም የውሃ ብክለትና ብክነት በመቀነስ፣  ዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ስርዓት በመዘርጋት እንዲሁም ቋሚና አላቂ ንብረቶችን በአግባቡ በማስተዳደር የውሃ አቅርቦት ስራን ዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። በፈረንጆቹ 2014 የተጀመረው ፕሮጀክቱ በመጪው ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም