አምቦ ዩኒቨርሲቲ በመጪው ቅዳሜ ከ5ሺህ በላይ ተማሪዎችን ያስመርቃል

149

አምቦ፣ጥር 20/2013 (ኢዜአ) አምቦ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ መስኮች ያሰለጠናቸውን 5ሺህ 73 ተማሪዎችን በመጪው ቅዳሜ እንደሚያስመርቅ አስታወቀ።

የዩኒቨርሲቲው ሪጅስትራር ዳይሬክተር አቶ ማንደፍሮ ለገሰ ለኢዜአ እንደገለጹት ተመራቂዎቹ በመደበኛና ተከታታይ መረሃ ግብሮች ትምህርታቸውን የተከታተሉ ናቸው።

ከተመራቂዎቹ መካከል 356 በሁለተኛ ዲግሪ፣ ስድስት በሶስተኛ ዲግሪ፣20 በህክምና ዶክተሬት እና ቀሪዎቹ በመጀመሪያ ዲግሪ የሰለጠኑ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በሶስተኛ ዲግሪ (ፒ ኤች ዲ) የሚያስመረቃቸው ስድስቱ ተማሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን አመልክተዋል።

ለትምህርት አሰጣጡ የሚያግዙና የኮሮና ወረርሸኝን ለመከላከል የጥንቃቄ እርምጃዎች ሲተገበሩ መቆየታቸውን ገልጸው፤ በአንድ ክፍል ከ30 ያልበለጡ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ መደረጉን አስረድተዋል።

በዚህም ዩኒቨርሲቲው ወረርሽኙን በመከላከል ያስተማራቸውን ከ5ሺህ በላይ ተማሪዎችን ጥር 22/2013 ዓ.ም ለማስመረቅ መዘጋጀቱን ነው የጠቀሱት። ከተመራቂዎቹ መካከል 1 ሺህ 640 ሴቶች መሆናቸውም ተመልክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም