አጠቃላይ፣ አገር በቀልና አካታች የትምህርት ቤት ምገባ መርሃግብር ይፋ ሆነ

80

አዲስ አበባ፣ ጥር 19/2013 ( ኢዜአ) በአገሪቷ አምስት ክልሎች ለአንድ ዓመት የሚተገበር አጠቃላይ፣ አገር በቀልና አካታች አዲስ የትምህርት ቤት ምገባ መርሃግብር ይፋ ሆነ። 

ትምህርት ሚኒስቴር ከሕፃናት አድን ድርጅት ጋር ይፋ ያደረገው መርሃ ግብሩ በ21 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ለአንድ ዓመት የሚተገበር ነው።

መርሃግብሩ በአፋር፣ በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌና በሲዳማ ክልሎች በሚገኙ 13 ወረዳዎች በሚገኙ 499 ትምህርት ቤቶች  ነው የሚተገበረው።

በዚህም በቅድመ መደበኛ እና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ከ163 ሺህ በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።

ለትግበራው የሚያስፈልገው በጀትም በ'ዓለም አቀፍ ትብብር ለትምህርት'መመደቡም ተገልጿል።

የህፃናት አድን ድርጅት የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ኢኪን ኦጎቶጉላሪ እንዳሉት ድርጅቱ ከሚሰራባቸው ፕሮጀክቶች አንዱ የትምህርት ዘርፍ ነው።

ተማሪዎች ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩና መጠነ ማቋረጥን ለመቀነስ የተማሪዎች ምገባ ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።

ይፋ የተደረገው መርሃግብር በተመረጡት አምስት ክልሎች የሚገኙ ሴቶችን፣ አካል ጉዳተኞችን፣ ስደተኞችንና በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ሰዎችን ተጠቃሚ ያደርጋል ብለዋል።

ድርጅቱ ለዘርፉ የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

የትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በተለያዩ ክልሎች 1 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በመመደብ 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተማሪዎችን ለመመገብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

መርሃግብሩ ላለፉት ዓመታት ሲተገበር የቆየውን አገር በቀል የትምህርት ምገባ ለማጠናከር የሚያግዝ እንደሆነም ተናግረዋል።

የመርሃግብሩ ተጠቃሚዎችን መመልመያ የሆኑት በታዳጊ ክልሎች የሚገኙ፣ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ያሉና ተዛማጅ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የትምህርት ምገባው ተማሪዎች ትምህርታቸውን በብቃት መከታተል የሚያስችልና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያግዝና ወደፊትም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል።

መርሃግብሩ በቀጥታ ተጠቃሚ ከሚያደርጋቸው በተጨማሪ 500 ሺህ አርሶ አደሮችን በተዘዋዋሪ መንገድ ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም