ኤምባሲው ከ73ሺ ዶላር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ግብዓቶችን ለሰላም የህጻናት መንደር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ

99

አዲስ አበባ፣ ጥር 19/2013 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ከ73ሺ ዶላር በላይ የሚያወጡ የተለያዩ ግብዓቶችን ለሰላም የህጻናት መንደር ድጋፍ እንደሚያደርግ ገለጸ። 

በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ኢቶ ታካኮ እና የሰላም የህጻናት መንደር ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ጫሊ ድጋፉን በሚመለከት ዛሬ ስምምነት ተፈራርመዋል።

አምባሳደር ኢቶ ታካኮ በዚህን ወቅት ጃፓን በሥራ ዕድል ፈጠራ እና በሴቶች ተጠቃሚነት ላይ ያላትን ልምድ ለኢትዮጵያ ማካፈል እንደምትሻ ገልጸዋል።

ጀፓን እ.አ.አ 2014 በሰላም የህጻናት መንደር ውስጥ በተለያዩ ዘርፎች ሙያዊ ስልጠና እያገኙ ያሉ ሴቶችን ለማገዝ ድጋፍ ማድረጓንም ነው ያስታወሱት።

በወቅቱ የተደረገው ድጋፍ በስልጠና ላይ ያሉ ሴቶች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ብቁ በማድረግ ረገድ ሚናው የጎላ እንደነበርም አምባሳደሯ ገልጸዋል።

ኤምባሲው የሴቶቹን ተጠቃሚነት በተሻለ መልኩ ለማጠናከር ከ73ሺህ 300 ዶላር በላይ ወጪ የተደረገባቸውን የተለያዩ ግብአቶች ለማዕከሉ ድጋፍ እንደሚያደርግም ቃል ገብተዋል።

ድጋፍም በዋናነት በሰላም የህጻናት መንደር ውስጥ ያለውን ስልጠና ማዕከል ለማሟላት የሚውል መሆኑንም አብራርተዋል።

የማዕከሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ጫሊ በበኩላቸው ኤምባሲው ከዚህ ቀደም ያደረገው ድጋፍ በርካታ ሴቶች የስራ እድል እንዲያገኙ ማገዙን አንስተዋል።

ከዚህ አንጻር ቃል የተገባው ድጋፍ የማዕከሉን አቅም ከማሳደግ አኳያ ሚናው የጎላ መሆኑን ነው የተናገሩት።

በተለይ ተጨማሪ ሴቶች የጨርቃጨርቅ ስልጠና ወስደው የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ እንደሚያግዝም  ጨምረው ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የጃፓን ኤምባሲ ለማዕከሉ በየጊዜው እያደረገ ላለው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

ሰላም የህጻናት መንደር ከተቋቋመ 35 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም ከ3ሺህ በላይ ወጣቶችና ከ2 ሺህ በላይ ህጻናት የሰብአዊ ድጋፍን ጨምሮ የተለያዩ እገዛዎችን  በመስጠት ላይ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም