በምዕራብ አርሲ ዞን በመጪው ክረምት የሚተከሉ 45 ሚሊዮን ችግኞች ተዘጋጅተዋል

55

አዲስ አበባ ጥር 19/2013 (ኢዜአ) በምዕራብ አርሲ ዞን በመጪው ክረምት በአረንጓዴ አሻራ ልማት የሚተከሉ 45 ሚሊዮን ችግኞች መዘጋጀታቸውን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ኃብት ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ አብደላ ኢብራሂም በመጪው ክረምት 250 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል መታቀዱን ለኢዜአ ገልፀዋል።

እንደ እርሳቸው ገለፃ በዞኑ አገር በቀል ችግኞች፣ ለእንሳስት መኖ የሚውሉና የተለያዩ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች እየተዘጋጁ ነው።

የችግኝ ዝግጅቱ ከሚከናወንባቸው የዞኑ ወረዳዎች መካከል አዳባ እና ነጌሌ አርሲ እንደሚገኙበት አቶ አብደላ ገልጸዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከተተከሉት 146 ሚሊዮን ችግኞች መካከል 84 በመቶዎቹ መፅደቃቸውንና ኅብረተሰቡም በባለቤትነት እየተንከባከባቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የአዳባ ወረዳ የእርሻና ተፈጥሮ ኃብት ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ግርማ ፈይሳ በበኩላቸው በወረዳው ዘንድሮ ለመትከል ከታቀደው 19 ሚሊዮን ችግኝ እስካሁን 4 ሚሊዮን ያህሉ መዘጋጀቱን ገልፀዋል።

በወረዳው ባለፈው ዓመት ከተተከሉ 9 ሚሊዮን ችግኞች 90 በመቶዎቹ መፅደቃቸውንም አክለዋል።

የነጌሌ አርሲ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳሎ መሃመድ በበኩላቸው በማኅበር በተደራጁ ወጣቶች፣ በግለሰቦችና በአርሶ አደር ማሰልጠኛ ተቋማት ችግኝ እየተዘጋጀ መሆኑን ገልፀዋል።

ባለፈው ዓመት በወረዳው 7 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኝ ተተክሎ ከ6 ሚሊዮን በላይ መፅደቁን ገልፀው በዚህ ዓመትም ከ25 ሚሊዮን በላይ ችግኞች ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በወረዳው በማኅበር ተደራጅቶ ችግኝ የሚያዘጋጀው ወጣት ጀማል አብዱሮ ባለፈው ዓመት ከ958 ሺህ በላይ ችግኞችን አዘጋጅተው በተለያዩ አካላት መተከላቸውን አስታውሷል።

በዚህ ዓመት በጣቢያው ከአንድ ሚሊዮን በላይ ችግኞችን እያዘጋጁ መሆኑንም ወጣቱ ገልጿል።

በዞኑ በ2004 ዓ.ም 22 በመቶ የነበረው የደን ሽፋን አሁን ወደ 33 በመቶ ከፍ ማለቱን ማወቅ ተችሏል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም