ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከስደት ለተመለሱ 140 ዜጎች የስራ እድል አመቻቸ

94

ሐረር፤ጥር 19/2013(ኢዜአ ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ከስደት ለተመለሱ 140 ዜጎች የሥራ እድል ማመቻቸቱን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው ከአለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት / አይ ኦ ኤም/ ጋር በመተባበር  የስደት ተመላሾች የስራ እድል እንዲያገኙ እያከናወነ ያለውን ሥራ እየተገመገመ ነው።

በዩኒቨርሲቲው የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የስደት ተመላሾችን መልሶ ማቋቋም አስተባባሪ  ዶክተር  ከተማ በቀለ እንደገለጹት ከአለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት ጋር በዞኑ ከስደት  የተመለሱ ዜጎችን ወደ ስራ ለማስገባት የተቀናጀ ስራ ሲያከናውኑ ቆይተዋል።

ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር በተከናወነው ሥራ በዞኑ 12 ወረዳዎች 140  ተመላሽ  ዜጎች የማሀበራዊ፣ስነ ልቦናዊና እና የንግድ ክህሎት ስልጠና በመስጠት የሥራ እድል  እንደተመቻቸላቸው ተናግረዋል።

ንግድ፣ እንስሳት እርባታና ማደለብ  እንዲሁም ኤሌክትሮክስ ጥገና   ከተመቻቸላቸው  የሥራ እድል ውስጥ እንደሚገኙበት ዶክተር ከተማ ጠቅሰው በዚህም ከጠባቂነት  በመላቀቅ እራሳቸውን እየቻሉ መሆኑን አሰረድተዋል።

ለዚህም የአለም አቀፉ የፍልሰት ደርጅት ዘጠኝ ሚሊዮን 400 ሺህ ብርድጋፍ  ማደረጉን  አመልክተዋል።

የሥራ እድል ከተመቻቸላቸው ተመላሾች መካከል በዞኑ በደኖ ወረዳ የአኒሳ ቀበሌ  ገበሬ  ማህበር ተወላጅ  ወጣት ጃለታ ሙክታር በሰጠው አስተያየት  76 ወጣቶች  ሆነው  በድሬዳዋ  ጅቡቲ አድርገው ወደ ሳኡዲ በተጓዙበት ወቅት  በርሃብና  በበሽታ   24 ጓደኞቻቸው  በመንገድ ላይ ህይወታቸው ማለፉን አስታውሷል።

በአለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት አማካኝነት ወደ ሀገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከሐረማያ  ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባደረገላቸው 40 ሺህ ብር ድጋፍ ወደ ከብትማ ድረብ ሥራ  ተሰማርቶ ውጤተማ መሆናቸውን ተናግሯል።

"በጅቡቲ በኩል ነበር ወደ የመን የሄድኩት፤ በረሃብና ስቃይ  ጓደኞቼን በእጄ ላይ ህይወታቸው አልፎ ቀብሬያለው" ያለው ደግሞ ሌላው  የበደኖ  ወረዳ ገነሚ ቀበሌ  ተወላጅ ወጣት አህመድ መሐመድ ነው።

በአሁኑ ወቅትም ባገኙት የገንዘብ ድጋፍ ወደ ቡና ንግድ ስራ በመግባት ህይወቱን  እየለወጠ እንደሚገኝ ገልጾ  ወጣቶች በህገ ወጥ ደላሎች እየተታሉ ወደ ውጭ ከመሄድ  ይልቅ በሀገራቸው ሰርተው መለወጥ እንደሚችሉ ከእነሱ መማር እንዳለባቸው  ተናግሯል።

እንደ ወጣቶቹ ገለጻ የስራ እድል በማገኘት ተጠቃሚ ቢሆኑም አሁንም ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ  ከስደት የተመለሱ ወጣቶች ላይ በትኩረት መሰራት ይኖርበታል።

የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት የህገወጥ ስደት መካለከል የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ደለለኝ ረታ እንዳሉት በኮሮና ምክንያት በአለም አቀፍ  የፍልሰት ድርጅት በኩል 1ሺህ 150 ዜጎች ከስደት   ወደ ዞኑ ተመልስዋል።

ወደ ሥራ ላልገቡ ለቀሪዎቹም ለማመቻቸት ከወረዳ የስራ እድል ፈጠራ  ጋር  በመነጋገር  ሥልጠና በመሰጠት ላይ መሆናቸውን  ገልጸዋል።

በዩኒቨርሲቲው መሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው የግምገማው መድረክ  የዞንና   ወረዳ  የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት አመራሮች እንዲሁም ከስደት  ተመልሰው  ውጤታማ የሆኑ ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም