በስድስት ወር ለ384 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል-ቢሮው

116

ባህርዳር ጥር 19/2013 (ኢዜአ) ባለፉት ስድስት ወራት ለ384 ሺህ ወጣቶች የስራ ዕድል መፈጠሩን የአማራ ክልል የቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞልች ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ የስራ ዕድል ፈጠራ ግብረ ኃይል የንቅናቄ መድረክና የ2013 ግማሽ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ በደብረ ታቦር ከተማ አካሂዷል።

የቢሮው ኃላፊ አቶ አረጋ ከበደ በወቅቱ እንደገለጹት በበጀት አመቱ ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ለሚበልጡ ወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠር ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።

በግማሽ ዓመቱ  በገጠርና በከተማ ለሚገኙ ለ384 ሺህ ወጣቶች እድሉን መፍጠር እንደተቻለ ተናግረዋል።

ለወጣቶቹ የስራ ዕድሉ የተፈጠረው በማኒፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በእንጨትና ብረታብረት፣ በግብርና፣ በአገልግሎትና በሌሎች ዘርፎች እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በተፈጠረው የስራ እድል የግማሽ አመቱን እቅድ 64 በመቶና የበጀት አመቱን 32 በመቶ ክንውን መመዝገቡን አመልክተዋል።

"በባለድርሻ አካላት የቅንጅት መጓደልና በወቅታዊ ችግሮች ተጽዕኖ  በተያዘው እቅድ ልክ  አፈፃፀም ማስመዝገብ አልተቻለም" ብለዋል።

ለበጀት ዓመቱ 2 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ብድር ለመስጠት ታቅዶ  40 ሚሊዮን ብር ብቻ ማሰራጨት መቻሉ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንዲሆን ያደረገው ሌላውና ዋናው ምክንያት እንደሆነ ጠቅሰዋል ።

"ቀደም ሲል በተዘዋዋሪ ፈንድ ለወጣቶች የተሰራጨ ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ዞኖች ማስመለስ ባለመቻላቸው ችግሩ ተፈጥሯል" ብለዋል።

በመሆኑም ለስራ እድል ፈጠራ እንቅፋት የሆኑ ችግሮችን በተደራጀ አግባብ በመፍታት የዓመቱን እቅድ ሙሉ በሙሉ ለመሳካት ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል።

የክልሉ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊና የስራ ዕድል ፈጠራ ግብረ ኃይል ሰብሳቢ ዶክተር ሰይድ ኑሩ በበኩላቸው በክልሉ 19 ነጥብ 6 በመቶ ስራ ፈላጊ ወጣቶች መኖራቸውን ተናግረዋል።

መዋቅራዊ ለውጥ ሊያመጣ በሚችል መልኩ የስራ ዕድል መፍጠር አለመቻሉን ጠቁመው "ስራ አጥ ወጣት ይዞ የሚጠበቀውን ዕድገት ማምጣት አይታሰብም" ብለዋል።

"ከፊታችን የተደቀነውን የስራ ዕድል ፈጠራ ችግር ለመሻገር ቀደም ሲል በተዘዋዋሪ ብድር ለወጣቶች ተሰጥቶ ያልተመለሰን ገንዘብ ማስመለስ ግድ ይላል" ብለዋል።

በየደረጃው ያለው ዓመራር፣ ባለድርሻ አካላትና የስራ ዕድል ፈጠራ ግብረ ሃይል በመቀናጀት የተሰራጨውን ብድር በማስመለስ ስራ ለሌላቸው ወጣቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

በክልሉ ባለፈው ዓመት ከ980 ሺህ ለሚበልጡ ወጣቶች በተለያዩ ዘርፎች የስራ ዕድል መፍጠር እንደተቻለ ከቢሮው የተገኘ መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም