የዓለምአቀፉ የንፁሃን የጅምላ ዘር ጭፍጨፋ ሰለባዎች ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው

135

ጥር 19 / 2013 (ኢዜአ) የዓለምአቀፉ የንፁሃን የጅምላ ዘር ጭፍጨፋ ሰለባዎች ቀን በአዲስ አበባ እየተከበረ ነው።

ይህ ዕለት (January 27) በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረወ ከዛሬ 76 ዓመት በፊት በአዶልፍ ሒትለር መራሹ የጀርመን የበላይነት አቀንቃኝ ናዚ ቡድን በአይሁዳውያን ላይ የተፈፀመውን ጅምላ ጭፍጨፋ መሰረት በማድረግ ነው።

እ.አ.አ ከ2005 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ይከበራል። በአዲስ አበባ የእስራኤልና የጀርመን አምባሳደሮችን ጨምሮ የየመንግሥታቱ ድርጅት ተወካዮች ባሉበት በኢሲኤ እየተከበረ ነው።

ከዛሬ 76 ዓመት በፊት 6 ሚሊየን አይሁዳውያን በአውሮፓ ምድር በጅምላ የተጨፈጨፉበትና ሌሎች ሚሊዮኖች የተገደሉበት ጊዜ ነበር።

በመድረኩ የጀርመኑ አምባሳደር ስቴፈን “ጀርመን በናዚ የተፈፀመውን ጭፍጨፋ ዕውቅና ትሰጠዋለች፣ በታሪክም ወንጀሉን ለልጅ ልጆቻችን ዳግም እንዳይደገም እንዘክራለን” ብለዋል።

የፀረ ፅዮናዊያን እንቅስቃሴንም አጥብቃ እንደምታወግዝና እንደምትታገል አረጋግጠዋል።

የናዚ ድርጊት ጥላቻ፣ ዘር ማጥፋት፣ አክራሪ ብሔርተኝነትን በግለሰብ ደረጃም ሆነ ቡድን ማስወገድና አብሮነትና መቻቻልን ማጎልበት እንደሚገባ ከታሪክ መማር እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሁለቱ አገሮች ለትናንት ዕውቅና ሰጥተው የወደፊት በጋራ ግንኙታቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል።

የእስራኤሉ አምባሳደር ራፋኤል ሞራቭ በበኩላቸው “ከ6 ሚሊየኖች ንፁሃን አይሁዳውያን ጭፍጨፋ አስከፊነት በማስታወስ ዛሬ የዘር ተኮር ጥላቻና ዘር ማጥፋትን ለማስወገድ በጋራ መስራት ይገባል” ብለዋል።

“ዕለቱን ከጀርመን ጋር ስንዘክር አንድም የይቅርታን ኃይል፣ አንድም ከታሪክ በመማር ለሰው ልጅ ዕኩል ክብር መስጠት እንደሚገባ ለማሳየት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

“ቀኑን በዚህ አግባብ ለቀጣይ ትውልድ እንዘክራለን” ነው ያሉት።በመድረኩ ከጥቃት የተረፉ ሰዎች በስካይፒ ትውስታቸውን አጋርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም