በመተከል ዞን በሁለት ቢላዋ የሚበሉ የጸጥታ ሃይል አባላት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ማሳሰቢያ ተሰጠ

161

ጥር 19 ቀን 2013 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተጣለባቸውን የህዝብ አደራ ችላ በማለት የሽፍታውን እንቅስቃሴ እያገዙ 'በሁለት ቢላዋ የሚበሉ' የጸጥታ መዋቅሩ አባላት አካሄዳቸውን ማስተካከል እንዳለባቸው ማሳሰቢያ ተሰጠ።

በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን ለሚሰሩ የጸጥታ ሃይል አመራሮችና አባላት ስልጠና እየሰጠ ነው።

በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው ግብረ-ሃይል በዞኑ ከሚገኙ የተለያዩ ማህበረሰብ ክፍሎች ጋር ባደረገው ውይይት በዞኑ በተከሰተው የጸጥታ ችግር ላይ አንዳንድ የጸጥታ ሃይል አባላት እጃቸው እንዳለበት መገንዘቡን አስታውቋል።

በመሆኑም በዞኑ የሚሰራው የጸጥታ ሃይል አመራሮችና አባላት እንዲገመገሙና ሥልጠና እንዲወስዱ እየተደረገ ነው።

ከጋንታ መሪ እስከ ብርጌድ አዛዥ የነበሩ 109 ፀረ-ሽምቅ፣ ልዩ ጥበቃና አድማ ብተና ልዩ ኃይሎች እንዲሁም በዞኑ በየደረጃው የሚገኙ 37 የፖሊስ አመራሮች ስልጠናውን መውሰድ ጀምረዋል።

የምዕራብ ዕዝ ምክትል አዛዥና የግብረ-ሃይሉ አባል ብርጋዴል ጄነራል ዓለማየሁ ወልዴ እንዳሉት፤ የጸጥታ ኃይሉ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችን በእኩልነትና በተዓማኒነት የማገልግል ሃላፊነት አለበት።

ከዚህ በተቃራኒ የሚደረጉ ማናቸውንም አይነት ህገ-ወጥ እንቅስቃሴ በፍጥነት መቆም እንዳለበትም ነው ያሳሰቡት።

"የህዝብ አገልጋይ መስለው የሽፍታውን እንቅስቃሴ እያገዙ 'በሁለት ቢላዋ ለመብላት' ሲነቀሳቀሱ የነበሩ የጸጥታ መዋቅሩ አባላት አካሄዳቸውን ማስተካከል አለባቸው" ብለዋል።

"ማንኛውም የጸጥታ ኃይል ከህዝብና አገር በታች መሆኑን አስገንዝበው፤ የተዘበራረቀ አስተሳሰብ የሚያራምዱ የጸጥታ መዋቅር አባላት ቆም ብለው መስመራቸውን ሊያጠሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።

በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኦፕሬሽን ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ኢሳቅ አሊ የጸጥታ ኃይሎች ከፖለቲካ ፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ ሆነው ሃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።

የፖሊስ ተልዕኮ ህገ-መንግስቱንና ህገ-መንግስታዊ ሥርዓቱን ማክበርና ማስከበር መሆኑን ጠቅሰው፤  ከዚህ ተልዕኮ ውጭ ሌላ ዓላማ ያነገቡ የጸጥታ ኃይሎች ራሳቸውን እንዲፈትሹ አሳስበዋል።

"የክልሉ የፖሊስና ልዩ ኃይል አባላት በህብረተሰቡ ዘንድ ይነሳባቸው የነበረውን ቅሬታ በእኩልነት በማገልገልና አካባቢውን ሰላማዊ በማድረግ መካስ አለባቸው" ብለዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኢሳቅ አብዱልቃድር በበኩላቸው ከፖሊስ የሚጠበቀው ከወገንተኝነት ነጻ በሆነ መልኩ ሳይንሱን መተግበር ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

"ጸጥታ ሃይሉ በዞኑ የተፈጸመው መጥፎ ድርጊት እንዳይደገም በሃላፊነት መስራት አለበት" ሲሉም ሃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም