ወጣቶች የሚፈልጓትን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ሚናቸውን መወጣት አለባቸው --ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል

86

አሶሳ ፤ ጥር 18 / 2013( ኢዜአ) ወጣቶች የሚፈልጓትን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ከጠባቂት በመላቀቅ ሚናቸውን መወጣት እንዳለባቸው የሠላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ተናገሩ፡፡

ከአምስት ክልሎች ለተውጣጡ የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የተዘጋጀ የ45 ቀናት ሥልጠና ዛሬ በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ተጀምሯል፡፡

ሥልጠናው ሲጀመር የሠላም ሚኒስትሯ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ባስተላለፉት መልዕክት ላይ  እንዳሉት ሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀገሪቱ የበለጸገች እና ዴሞክራሲ የተረጋገጠባት እንድትሆን ይፈልጋል፡፡

ይህ ደግሞ በፍላጎት ብቻ የሚሆን አይደለም ያሉት ሚኒስትሯ በተለይም ወጣቶች የራሳቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ተናገረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች በበጎ ፈቃድ ተግባር እንዲሰማሩ በማድረግ ለዜጎች ተጠቃሚነት በሚከናወኑ ተግባራት ላይ አሻራቸውን እንዲያሳርፉ ለማገዝ ሥልጠናው ማዘጋጀቱን አስረድተዋል፡፡

ሥልጠናው በጎ ፈቃደኛ ወጣቶቹ አቅማቸውን በማጎልበት አዳዲስ እውቀት በመሸመት ሌሎችን መርዳት ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

ከሥልጠናው ተሳታፊዎች መካከል ወጣት መሃመድ ሬድዋን በተለይ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ሥልጠናውን ለመከታተል ወደ አካባቢው  በገባበት ባለፉት ሶስት ቀናት የአካባቢው ማህበረሰብ በርካታ ቋንቋዎች እንደሚያወራ እና ተፈቃቅሮ እንደሚኖር መረዳቱን ገልጿል፡፡

በሥልጠናው ብቻ ሳይሆን ከአካባቢው ባህል በጎ ነገር ጭምር ቀስሞ እንደሚመለስ ተስፋ ማድረጉን ተናግሯል፡፡

ወጣት ሃና በላይ በበኩሏ በ45 ቀናት ቆይታችን የሃገራችንን አንድነት ለማጠናከር የሚያግዝ መሰረታዊ ግንዛቤ እናገኛለን የሚል እምነት አለኝ ብሏል፡፡

በሥልጠናውን መድረክ የተገኙት  የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ ባደረጉት ንግግር ሥልጠናው ብሔራዊ መግባባትን በማስፈን የተዋሃደች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ያግዛል ብለዋል፡፡

ቢሮው ሥልጠናው እስኪጠቀቅ አስፈጊውን እገዛ እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ከማል አብዱራሂም በበኩላቸው የሕይወት ክህሎት፣ የዜግነት መብት እና ማህበራዊ ጸጋ፣ የመገናኛ ዘዴ አጠቃቀም፣ መግባባት እና ብዝሃነት፣ ስራ ፈጠራ እና የስራ እድል፣ እንዲሁም የማህበረሰብ አገልግሎት የሥልጠናው ዋነኛ ትኩረቶች እንደሆኑ ገልጸዋል፡፡

ሥልጠናው ህይወታቸውን  ለማሻሻል ብሎም ለሀገሪቱም ሠላም ትልቅ ፋይዳ ያለው በመሆኑ   በአግባቡ እንዲከታተሉም መልዕክታቸውን አስተላለፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም