በምዕራብ አርሲ ዞን በመስኖ ስንዴ የመልማት አቅም ላላቸው አካባቢዎች የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ተከፋፈሉ

227

አዲስ አበባ ጥር 18/2013 (አዜአ) በምዕራብ አርሲ ዞን በመስኖ ስንዴ የመልማት እምቅ አቅም ላላቸው አካባቢዎች ከ300 በላይ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች መከፋፈላቸውን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበራ ቡኖ ተናገሩ።

በዞኑ በትራክተር የማረስ፣ በኮምባይነር ሰብል የመሰብሰብና፣ በመስኖ የማልማት እንዲሁም በኩታ ገጠም የእርሻ ስራዎች በስፋት በመከናወን ላይ ናቸው።

በዞኑ 87 ትራክተሮች በመንግስት ድጎማ ተገዝተው እያረሱ ሲሆን በ26 ኮምባይነሮች ደግሞ ምርት የመሰብሰብ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በዞኑ በዚህ ዓመት ከተገኘው ከ11 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት 85 በመቶው በኮምባነር የተሰበሰበ መሆኑንም ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በመስኖ ስንዴ ለማልማት በተያዘው አቅድ መሰረት በዘመናዊ፣ ባህላዊና በውሃ መሳቢያ ፓምፖች በመጠቀም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አቶ አበራ ተናግረዋል።

በመስኖ ስንዴ የመልማት እምቅ አቅም ላላቸው አካባቢዎች ከ300 በላይ የውሃ መሳቢያ ፓምፖች ለ9 ወራዳዎች መከፋፈላቸውንም አቶ አበራ ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ገበያ መር የሆኑ ምርቶችን እያመረተ ከፋብሪካዎች ጋር ትስስር እየተፈጠረ ይገኛልም ብለዋል።

የቢራ ገብስና የስንዴ ምርትን ለፋብሪካዎች በስፋት እያቀረቡ ሲሆን በዚህም የውጭ ምንዛሬን ለማስቀረት የሚደረገውን ጥረት እያገዙ ይገኛሉ ብለዋል።  

በዞኑ በዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ በመጠቀምና በቴክኖሎጂ በመታገዝ የግብርና ስራው ስፋት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የግብርና ባለሙያዎችም ከአርሶ አደሩ ጋር በቅርበት እየሰሩ ነው ብለዋል።

በዞኑ የአዳባ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር እሼቱ ታደስ እንዳሉት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ በስፋት እየተተገበረ በመሆኑ የተሻለ ምርት እያገኙ ነው።

ከዚህ በፊት በነበራቸው አሰራር በሄክታር በአማካይ 15 ኩንታል ያገኙ የነበረውን አሁን ላይ እስከ 40 ኩንታል እያገኙ መሆኑን ገልጸዋለ።

የሄበን አርሲ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ገመቹ ቡላ እንዳሉትም ዘመናዊ ግብዓቶችን በመጠቀማቸው የተሻለ ምርት እያገኙ ነው።

በአሁን ላይ ከባለሙያ የሚሰጣቸውን ምክርና ድጋፍ በመጠቀም ወደ ማካናይዝድ የአስተራሰስ ዘዴ መግባታቸውን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም