የገጠር ቀበሌዎቹ ከፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች የኤሌክትሪክ አገልግሎት አግኝተዋል

108

አዲስ አበባ ጥር 18/2013 (ኢዜአ) በአራት የገጠር ቀበሌዎች የተገነቡ የፀሐይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ገለፀ።

ግንባታቸው በ2012 በጀት ዓመት ከተጀመረው 12 የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መካከል በአራት የገጠር ቀበሌዎች የተጠናቀቁት አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን አገልግሎቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል በሶማሌ፣ በኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በጋምቤላ ክልሎች በሚገኙ ቀበሌዎች የተገነቡት ፕሮጀክቶች ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ለኅብረተሰቡ የኤሌክትሪክ አገልግሎት እየሰጡ ነው።

ቀሪዎቹንና በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብና በትግራይ ክልሎች የሚገነቡትን ስምንት የገጠር ከተሞችና መንደሮች ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ሲሆን አፈፃፀማቸው ከ46 እስከ 95 ነጥብ 5 በመቶ ደርሷል።

በድምሩ 3 ነጥብ 8 ሜጋ ዋት ኃይል ያመነጫሉ የተባሉት 12 የፀሃይ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አጠቃላይ ወጪ በዓለም ባንክ 8 ሚሊዮን 516 ሺህ 758 ዶላር እና በኢትዮጵያ መንግስት 59 ሚሊዮን 614 ሺህ 998 ብር ይሸፈናል።

ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቁ ከ71 ሺህ በላይ ደንበኞችን ተጠቃሚ በማድረግ፤ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ አስተዋፅኦ ይኖራቸዋል።

በየአካባቢዎቹ የሚገኙ የጤና ተቋማት፣ የእርሻ ማዕከላት፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወፍጮ ቤቶች፣ የውሃ ተቋማትና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የኤሌክትሪክ ተጠቃሚ ያደርጋሉም ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በቀጣይ ከዋናው የኃይል ቋት የሚርቁ 25 የገጠር ከተሞችና መንደሮችን በሚኒ ግሪድ የሶላር ፕሮጀክት ተጠቃሚ ለማድረግ ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን ጠቅሷል።

የኤሌክትሪክ ኃይል ተደራሽነትን ለማስፋትና በአገሪቷ ሁሉም አካባቢዎች የሚኖረውን ኅብረተሰብ እ.አ.አ 2025 ከዋናው የኃይል ቋት 65 ከመቶ፤ በአማራጭ የኃይል ምንጭ ደግሞ 35 ከመቶ ተጠቃሚ ለማድረግ አገራዊ የኤሌክትሪፊኬሽን ፍኖተ ካርታ ነድፎ እየሰራ መሆኑንም ገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም