የፌደራል፣ የክልልና ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች የጋራ ምክክር መድረክ ተጠናቀቀ

77

አዲስ አበባ ፣ጥር 18/2013 ( ኢዜአ) በላልይበላ ከተማ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የነበረው የፌደራል፣ የክልልና ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች የጋራ ምክክር መድረክ ተጠናቋል።

በመድረኩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምስት አመት እስትራቴጂክ እቅድና የፌደሬሽን ምክር ቤት የሪፎርም መርሃ ግብር ላይ ውይይት ተካሂዷል።

በቀረቡት ሰነዶች ላይ መጨመር ያለባቸውና ድጋሚ መታየት ባለባቸው ጉዳዮች ላይም ከተሳታፊዎች ግብአት ተሰብስቧል።

በተጨማሪም በጸደቀው የመንግስታት ግንኙነት አዋጅ አተገባበር ላይ ግንዛቤ ለመፍጠርና የጋራ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

በነዚህና ሌሎች የምክር ቤቶች ተግባር ላይ ውይይት የተካሄደ ሲሆን የህዝቦችን አንድነት ለማጠናከርና ዜጎች በነጻነት የሚኖሩባት ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ የተቀናጀ ጥረት እንደሚያስፈልግ በስፋት ተነስቷል።

ከመሰረተ ልማት፣ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት፣ የሰብአዊ መብት ጉዳይ ፣ የእኩልነት መረጋገጥ አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ስድስተኛው ጠቅላላ አገራዊ ምርጫ ዴሞክራሲያዊና ነጻ ሆኖ እንዲጠናቀቅም የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ መንግስት፣ የጸጥታ አካላትና ሌሎች ተዋናዮች የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቧል።

የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አደም ፋራህ በማጠቃለያ ንግግራቸው “ኢትዮጵያዊያን ከሚያለያዩን ይልቅ አንድ የሚያደርጉን ጉዳዮች በርካታ ናቸው በነሱ ላይ እናተኩር” ብለዋል።

የዜጎች ክብርና ሰብአዊ መብት መከበር ላይ በትኩረት መሰራት አለበት ያሉት አፈ ጉባኤው “በኢትዮጵያ በማንነቱ ምክንያት በየትኛውም አካባቢ ጭቆና ሊደርስበት አይገባም” ብለዋል።

ለዚህም ምክር ቤቶች ተቀናጅተውና ተግባብተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

አሁን ያሉ ምክር ቤቶች በቀጣይ ለሚመጡት የተጠናከረና ስማቸውን የሚያስጠራ አሰራርና አደረጃጀት ፈጥረው መሄድ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

በመድረኩ የነበሩ ውይይቶች ላይ የጋራ መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮችን እንደየ ክልሎች ተጨባጭ ሁኔታ እስከታችኛው መዋቅር ተግባራዊ እንዲደረግም አሳስበዋል።

በነዚህና ሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር መድረኩ ዛሬ ከሰአት በፊት የተጠናቀቀ ሲሆን የቀጣዩ መድረክ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል አርባ ምንጭ ከተማ ይካሄዳል ተብሏል።

የሴቶች ኮከስ ደግሞ ዛሬ ከስአት ጀምሮ በዚሁ በላልይበላ ከተማ የሚካሄድ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም