ምርጫው ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ እንዲሳካ ከወዲሁ መስራት እንደሚገባ ተመለከተ

67

ባህር ዳር፣ ጥር 18/2013( ኢዜአ) ቀጣዩ ሃገራዊና ክልላዊ ምርጫ ፍትሃዊና በህዝብ ዘንድ ተአማኒ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ ከወዲሁ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተመለከተ። 

ምርጫውን በሚመለከት ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ የእቅድ ዝግጅት ውይይት ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተጀምሯል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ አገኘሁ ተሻገር በውይይት መድረኩ እንዳሉት ምርጫው ሠላማዊ፣ ፍትሃዊ እና በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ መዋቅሩና የፖለቲካ ዘርፉ ከወዲሁ መሥራት ይጠበቅባቸዋል።

ምርጫው  እንዲሳካ ህዝብን ያሳተፈ ስራ ከወዲሁ ማከናወን እንደሚገባ አመልክተው፤ ማንም ያሸንፍ ማን  ዋናው ጉዳይ  ምርጫው በተአማኒነት  ህብረተሰቡ የፈለገውን እንዲመርጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር ነው ብለዋል።

ምርጫው እየተቃረበ ሲመጣ የክልሉን ሠላም  ለማደፍረስ የሚፈልጉ ሃይሎች ሊኖሩ ስለሚችሉ ቀድሞ በመለየት  ለማክሸፍ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የተጀመረው የብልፅግና ጉዞ ቀጣይነት ሊኖረው የሚችለው ህዝብ በነፃነት የፈለገውን መምረጥ ሲችል በመሆኑ ይህን ከግምት ውስጥ ያስገባ ስራ ይሰራል ሲሉ አቶ አገኘሁ አስታውቀዋል።

ለግማሽ ቀን በሚካሄደው የእቅድ ውይይት ላይ የዞን አስተዳዳሪዎችና የፀጥታ መዋቅሩ አመራሮች እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም