ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው-- የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን

62
ሰመራ ሀምሌ 17/2010 በክልሉ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያና የገንዘብ ዝውውርን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን የአፋር ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ። በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል የሥራ ሂደት አስተባባሪ ኮማንደር መሀመድ ኡትባን እንዳሉት በአገሪቱ እየተካሄደ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ ያልተመቻቸው አካላት ለውጡን ለመቀልበስ ሲጥሩ ይስተዋላል። ለእዚህም በተለያዩ አካባቢዎች ሁከትና ግርግር ለማስነሳት የጦር መሳሪያ በህገ ወጥ መንገድ ከማዘዋወር ባለፈ በተለያየ መንገድ ዶላር የማሸሽ እንቅስቃሴ በስፋት እየተስተዋለ መሆኑን ነው የገለጹት። የአፋር ክልል ከጅቡቲና ከኤርትራ ጋር በሰፊ ድንበር የሚዋሳንና የአገሪቱ ዋነኛ የገቢና ወጪ ንግድ ኮሪደር ጭምር በመሆኑ ለህገ ወጥ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውር ተጋላጭ መሆኑን አመልክተዋል። ችግሩን አስቀድሞ ለመከላከል ከክልልና ከፌዴራል ባለድርሻ አካካለት የተዋቀረ የጸረ ኮንትረሮባንድ ጥምር ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲሰራ መቆየቱን ኮማንደር መሀመድ አመልክተዋል። ኮሚቴው በዋነኛ የመውጫና የመግቢያ አካባቢዎች ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ባለፈ በየጊዜው በመገናኘት እየሰራ መሆኑ የገለጹት። ኮማንደር መሀመድ እንዳሉት ጥምረቱ ከክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከአገር መከላከያ ሠራዊት እንዲሁም ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት የተውጣጡ አካላትን የያዘ ነው። በየደረጃው የሚገኙ የክልሉ ጸጥታ ኃይሎችም ማህበረሰቡ በወንጀል መከላከል ተግባር በንቃት እንዲሳተፍ በማድረግ ራሱን ከህገወጥ ተግባር እንዲጠብቅና አካባቢውንም ነቀቶ በመጠበቅ ለአገራዊ ሰላም ጉልህ አስተዋጽኦ እንዲያበረከት ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። በተጨማሪም ክልሉ ከአጎራባች ክልሎች ጋር ያለውን ጠንካራ የህዝብ ለህዝብ ትስስርና የጋራ ሰላምና ልማት ለማስቀጠል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ኮማንደር መሀመድ አመልክተዋል። " በተለይም ከአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች በቅርቡ እየተስተዋሉ የሚገኙ ተደጋጋሚ ግጭቶች ለህገ ወጥ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ዝውውር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ በመሆኑ ለችግሩ አፋጣኝ እልባት ለመስጠት የሁለቱ ክልል አዋሳኝ ዞኖች የጋራ ኮሚቴ አደራጅተው እየሰሩ ይገኛሉ" ብለዋል። የሰመራ ከተማ ነዋሪ አቶ ኢጋህሌ አሊ በበኩላቸው የአገሪቱን  ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን እንደሚያወግዙ ተናግረዋል። በተለይ የሕብረተሰቡን አብሮነትና የተጀመረውን የአንድነት ጉዞ በማወክ ግጭቶችን ለመፍጠር የሚያደረገውን እንቅስቃሴ በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ነው። ይህን ኃላፊነት የጎደለው አጸያፊ ተግባር ለመመከት የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ የህብረተሰቡ ተሳትፎም ወሳኝ በመሆኑ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል። የአካባቢያቸው ህብረተሰቡም ከዚህ በፊት ሲያደርግ እንደነበረው አካባቢውን ነቅቶ በመጠበቅና ከጸጥታ ኃይሎች ጋር ተቀራርቦ በመስራት ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ መሆኑንም አስረድተዋል። በአማራ ክልል የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደርና ጸጥታ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደስታ ይማም በበኩላቸው በዞኑ ከዚህ በፊት የነበሩ የዞን አመራሮች በአዲስ መተካታቸውን ገልጸዋል። ይህም በዞኑ አዋሳኝ አካባቢዎች ከሚገኙ የአፋር ክልል አመራሮች ጋር ግንኙነቱ እንዲላላና በየደረጃው የተዋቀሩ የሰላም ኮሚቴዎችን በብቃት ለመደገፍ ክፍተት መፍጠሩን ተናግረዋል። ይህን ተከትሎ በአዋሳኝ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ግጭቶችና የእንስሳት ዝርፊያ ቢከሰትም ለችግሩ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ከኦጎራባች አፋር ወረዳዎችና ዞኖች ጋር በጋራ ተቀራርቦ በመስራት ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት ጥረት መጀመሩን አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም