የትራንስፖርት ዘርፍ ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ ዕድገትና መዘመን በቅንጅት መሥራት አለባቸው... አቶ ደመቀ መኮንን

79

አዲስ አበባ፤ ጥር 18/2013(ኢዜአ) አገሪቷን በዘመናዊ የትራንስፖርት ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ ባላድርሻ አካላት ተናበውና ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን አሳሰቡ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የትራንስፖርት ዘርፉን የአስር ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።   

መሪ ዕቅዱ እስካሁን የታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና ዘርፉን ለማዘመን ታስቦ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ዘርፉ ለሁሉም የልማት ስኬት የጀርባ አጥንት መሆኑን የገለፁት አቶ ደመቀ፤ 'ትራንስፖርትን ማዘመን አገርን ማዘመን መሆኑን ሁሉም ሊገነዘበው ይገባል' ብለዋል።

ኃያላኑ አሜሪካና ቻይና አሁን ለደረሱበት የዕድገት ደረጃ በትራንስፖርት ዘርፍ ያስመዘገቡት ውጤት መሆኑ ልብ ሊባል እንደሚገባም አመላክተዋል።

በዚህ ጉዳይ መንግሥት ትክክለኛውን አቅጣጫ መያዙን አንስተው ለዘርፉ ከፍተኛ ኃብት ፈሰስ በማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለትራንስፖርት ዘርፍ የ10 ዓመት መሪ የልማት ዕቅድ ስኬት ሁሉም አካላት ተገቢውን ርብርብ ሊያደርግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ዘርፉ ተፅዕኖ ፈጣሪ ማድረግ የሚያስችል ሁነኛ መሣሪያ በመሆኑ ተገቢውን አመራርና የሰው ኃይል ሥምሪት መስጠትና ቅንጅታዊ አሰራር ማጠናከር ይገባልም ብለዋል።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ዳግማዊት ሞገስ እንደተናገሩት መሪ ዕቅዱ የአገሪቷን የትራንስፖርት ዘርፍ ዘመናዊና ተወዳዳሪ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።

የአገሪቷ የዕድገት ፍላጎትና መጪው የብልጽግና ደረጃ ታሳቢ ተደርጎ እንዲሁም የአገራት ተሞክሮ ተቀምሮ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።

በመሪ ዕቅዱ ዘርፉ ከፍተኛ ኃብት፣ እውቅትና ክህሎት የሚጠይቅ በመሆኑ የባለኃብቶች ተሳትፎ እንዲጎለብት ትኩረት መደረጉን ጠቁመዋል።

ለዘርፉ ቀጣይ ዕድገት የሚያስፈልጉ የቴክኖሎጂ የዲጂቲል ኢኮኖሚ ግንባታም አጽንኦት መሰጠቱን ገልጸው፤በተጨማሪም ዘላቂ የልማት ፋይናንስ ለመፍጠር በተለይም ለሎጂስቲክስና ለአቬሽን ልማት ዘርፎች ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።

እነዚህም ዘርፎች ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የማመንጨት አቅም እንዳላቸው ነው ሚኒስትሯ የጠቆሙት።

ስፋት ያላቸው የመሰረተ ልማት ዝርጋታዎች፣ የትራንስፖርት አገልግሎት የልማት ተጠቃሚነትና ማኅበራዊ አካታችነትም በዕቅዱ ትኩረት አግኝተዋል ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በገጠር መንገድ ልማትና ትራንስፖርት አቅርቦት የማመቻቸትና በከተሞች የሞተር አልባ ትራንስፖርት አማራጮችን ማስፋት ላይ ይሰራል ነው ያሉት።

በተለይም ልዩ ፍላጎት ላላቸው የኅብረተሰበ ክፍሎች ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ለድምፅና ለአየር ብክለት ምክንያት የሆኑ አሮጌ ተሽከርካሪዎችን ለመቀነስና ለማስወገድ የሚያስችሉ የሕግና የአሰራር ሥርዓቶች መመቻቸታቸውን አብራርተዋል።

በታዳሽ ሃይል በተለይም በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ ተሽከርካሪዎችን ለማስፋት የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ማስፋፊያ ሥራዎች ለመሥራት መታቀዱንም ገልጸዋል።

በዚህም ዘርፉ ምቹ፣ ከብክለት የፀዳና ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር የሚደረገውን አገራዊ ጥረት በእጅጉ እንደሚደግፍ ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም