የግንባታ ጥራትና መጓተት ችግሮች ለግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ማነቆ ሆነዋል - ኢንጅነር አይሻ መሀመድ

105

ሀዋሳ፣ ጥር 17/2013 (ኢዜአ) "የግንባታ ጥራትና መጓተት ችግሮች ለግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ እድገት ማነቆ ሆነዋል" ሲሉ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ አስታወቁ።

የግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍን በማዘመን አገራዊ ብጽግናን እውን ለማድረግ መጠቀም እንደሚገባም አመልክተዋል።

ኢንዱስትሪውን ለማዘመንና አገራዊ ፋይዳውን ለማሳለጥ የሚያስችል የመጀመሪያ ዙር አገራዊ የኮንስትራክሽን ንቅናቄ መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ተጀምሯል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጅነር አይሻ መሀመድ በወቅቱ እንደገለጹት፤ የግንባታ ኢንዱስትሪ ዘርፍ ግዙፍ ሀብት፣ ቴክኖሎጂ፣ ከፍተኛ የሰው ሀይልና ዕውቀት ስለሚጠቀም የኢትዮጵያን ብልጽግና ዕውን ለማድረግ የሚያስችል አቅም አለው።

ዘርፉ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ከሌሎች ዘርፎች በተሻለ ተግዳሮቶችን በመቋቋም አገሪቱን ወደ ፊት ለማሻገር ያስቻለ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዘርፉ የሚስተዋሉ የግንባታ ጥራትና መጓተት ችግሮች ለእድገቱ ማነቆዎች መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ኢንዱስትሪውን ካሉበት ተግዳሮቶች እንዲላቀቅ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን ከመዘርጋት ጀምሮ በርካታ ተግባራት ማከናወን እንደሚጠይቅ አመላክተዋል።

ዓለም ከካርበን ጋዝ ልቀት ወደ ሚያላቅቁ አረንጓዴ ከተሞች ግንባታ መሸጋገሩን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ "እኛም ዘመናዊ የግንባታ ቴክኖሎጂ ትሩፋትን አሻግረን እንድንመለከት ከወዲሁ መስራት ይጠበቅብናል" ብለዋል ።

"በአማካሪዎች፣ በተቋራጮችና በባለሃብቶች መካከል መልካም ግንኙነት በመፍጠር በዘርፉ የሚፈለገውን ለውጥ ለማምጣት ያስችላል" ያሉት ሚኒስትሯ፤ ለተግባራዊነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽ ስራዎች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ነገዎ በበኩላቸው በዘርፉ ከጥራት ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ በርካታ ችግሮች እንዳሉ ገልጸዋል።

የመንገድና ህንጻ ግንባታ ላይ ጥቅም ላይ ከሚውለው የግንባታ ምርት ግብአት ጀምሮ የጥራት ችግር መኖሩን ጠቁመዋል።

የጥራት ቁጥጥር ክፍተት መኖሩን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ የግንባታ ደረጃ ክፍተት በኮንስትራክሽን ስራዎች ላይ ጫና ማሳረፉን አመልክተዋል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም