ህገ ወጥ የሰዎችን ዝውውር ለመከላከል የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

1095

ደሴ፣  ጥር 17/2013(ኢዜአ) በደቡብ ወሎ ዞን እየተባባሰ የመጣውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከል የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ። ።

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሴቶች ህጻናት፤ ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የተውጣጣ ሉኡካን  ከዞኑና ደሴ ከተማ አስተዳደር አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።

 በደሴ ከተማ በተካሄደው የውይይት መድረክ የዞኑ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ ሉባባ አሊ ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት ህገ ወጥ ደላሎች ዞኑን እንደ መሸጋጋሪያ ድልድይ እየተጠቀሙበት ነው፡፡

ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍል ህጻናትን ጭምር እየታለሉ በህገ ወጥ መንገድ በቃሉ ደጋን፣ ባቲ  ወረባቦ እና ጭፍራ በኩል  ወደ  አረብ ሀገር ለመውጣት ሲሞክሩ እንደሚስተዋል ጠቅሰዋል፡፡

ህገ ወጥ ደላሎች ከፌደራል እስከ ወረዳ የጥቅም ትስስር ስላላቸው በቀላሉ ማስቆም አልቻልንም ብለዋል፡፡

የህግ ማዕቀፉም ለአስራር አስቸጋሪ በመሆኑ ወንጀለኞች በጥፋታቸው ልክ አለመቀጣታቸው ችግሩ እንዲባባስ ማድረጉን ጠቁመው ለመከላከል የሁሉንም ተቋምና ባለድርሻ አካላት ርብርብ ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በተያዘው የበጀት ዓመት ብቻ ከሁለት ሺህ 600 በላይ ወጣቶችና ህጻናት በህገ ወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሞክሩ  ተይዘው ወደ የቤተሰቦቻቸው እንዲመለሱ መደረጉንም ኃላፊዋ አስረድተዋል፡፡

በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ የተገኙ 23 ደላሎችም በቁጥጥር ስር ውለው ጉዳዩ በህግ እየታየ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

በተለይ በሴቶች ላይ የሚደርሰው ግፍ አሳሳቢ መሆኑን ጠቁመው፤ ለከፍተኛ ወጭ ከመዳረጋቸውም ባለፈ ከእይታ ለመሰውር በጨለማ ጭምር ጫካ ለጫካ ሲጓዙ ለጉዳት እየተዳረጉ ነው ብለዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ተወካይ ወይዘሮ አበባ አሰፋ በበኩላቸው ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ህጻናትና ወጣቶች በደላሎች ደሴ ከተማ እንደሚሰበሰቡ ጠቁመዋል፡፡

ለመከላከል ጥረት ቢደረግም በመረጃ እጦትና ጥቅም ትስስር በሚፈለገው ልክ መከላከል አለመቻሉን ጠቅሰው፤ ለዚህም ባለድርሻ አካላት ጠንካራ ቅንጅትና ትብብር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

ህገ ወጥ ደላሎች በሎጅስቲክ፤ ኢኮኖሚና በሌሎችም የፈረጠሙ በመሆናቸው ቢያዙ እንኳ በዋስትና በተለያዩ ምክንያቶች ይለቃቀሉ ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሉኡካን  ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙንትሃ ኢብራሂም  በአካባቢው በዘርፉ የተሰሩ ተግባራትን በተግባር ለማየትና ለመገምገም መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በሪፖርቱ የቀረቡ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ጥሩ ጎኑ እንዲቀጥልና ክፍተቶች ከታች እስከ ላይ ባሉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እንዲስተካከሉ አቅጣጫ ይቀመጣል፤ ክትትልም ይደረጋል ብለዋል፡፡

በተለይ አሳሳቢ እየሆነ የመጣውን ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር እልባት እንዲያገኝ ምክር ቤቱ ኃላፊነቱን ይወጣል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ክፍተት ያለባቸው የህግ ማዕፎችም እንዲስተካከሉና ሁሉም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጥረት እንደሚደረግ የተናገሩት  ወይዘሮ ሙንተሃ ተግባሩ ውስብስብና አስቸጋሪ በመሆኑ በተወሰኑ መስሪያ ቤቶች ብቻ መፍታት እንደሚያዳግት አስረድተዋል፡፡

ሁሉም የየድርሻውን ተወጥቶ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርን በማስቆም በዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሁለንተናዊ ችግር ማቃለል ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው  አባላት በደቡብ ወሎና ደሴ ከተማ አስተዳደሮች ለአራት ቀናት በሚያደርጉት ቆይታ በጤና ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ፣ ሴቶች ፣ህጻናትና ወጣቶች መምሪያዎች ዙሪያ የተሰሩ ተግባራትን በመስክ በመመልከት አጠቃላይ ግብረ መልስ እንደሚሰጡ ይጠበቃል፡፡