የምክር ቤቱ አባላት ኢትዮጵያዊያን በነጻነት ተዘዋውረው የሚሰሩባት አገር ለመፍጠር ሃላፊነታቸውን ሊወጡ ይገባል

1448

ጥር 17 ቀን 2013 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን በየትኛውም አካባቢ በነጻነት ተዘዋውረው የሚሰሩባትን አገር ለመፍጠር በየደረጃው የሚገኙ የምክር ቤት አባላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው ተጠቆመ።

የፌዴራል፣ የክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች የጋራ ምክክር መድረክ በላልይበላ እየተካሄደ ነው።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ በመድረኩ የመክፈቻ ንግግራቸው በመተከል ማንነትን መሰረት ያደረገ ጅምላ ጭፍጨፋና ግድያ የተፈጸመባቸውና የተፈናቀሉ ዜጎች ጉዳይ ትኩረት እንደሚፈልግ ጠቁመዋል።

“ለዚህም በየደረጃው የሚገኙ ምክር ቤቶች በዜጎች ላይ የሚደርሰውን የሠብዓዊ መብት ጥሰትና ግፍ ለማስቀረት በጋራ መስራት አለባቸው” ብለዋል።

ሰው እንደ ሰው የሚከበርባት እንዲሁም ተንቀሳቅሶ የመኖር መብቱ እውን የሚሆንባት አገር መፍጠር እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል።

“ለዚህ ደግሞ ምክር ቤቶች የበኩላችንን ሚና የምንወጣበት ወቅት ላይ ነን” ሲሉ በአፅንኦት አንስተዋል።

“የጥፋት ሃይሎች እየፈጸሙት ያለው አስነዋሪ ተግባር የኢትዮጵያን ሕዝብ የማይመጥን ነው” ያሉት አፈ-ጉባኤዋ፤ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የቀለምና ሌሎች ልዩነቶች ቢኖሩም ኢትዮጵያን መጠበቅ ግን ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ያከናወኑትን የለውጥና የአደረጃጀት ስራ ያብራረሩት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ “ምክር ቤቶች ውክልናቸውን በመወጣት የሕዝብ ወገንተኝነታቸውን በስራዎቻቸው ማረጋገጥ አለባቸው” ብለዋል።

የሕግ አወጣጥ ሂደት፣ የክትትልና ቁጥጥር ስራ እንዲሁም የሕዝብ ውክልናን ለማሻሻል በርካታ ስራዎች መከናወኑን ገልጸው፤ መጪው አገራዊ ምርጫ ነጻ፣ ፍትሃዊና ተዓማኒ እንዲሆን ሁሉም የምርጫ ተዋናዮች ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።

በላልይበላ እየተካሄደ ያለው የፌዴራል፣ የክልልና የከተማ አስተዳደሮች ምክር ቤቶች የጋራ ምክክር መድረክ ነገ የሚቀጥል ሲሆን በስትራቴጂክ ዕቅድ፣ በለውጥ ስራዎችና ሌሎች አጀንዳዎች ላይ ይመክራል።