በመተከል ዞን ከህግ ማስከበሩ በተጓዳኝ እርቅና አብሮነት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ ነው - ግብረ ሃይሉ

73

በመተከል ዞን በሽፍቶች ላይ እየተወሰደ ካለው የህግ ማስከበር እርምጃ ጎን ለጎን እርቅና አብሮነት ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራ መሆኑን በመንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረሃይል አስታወቀ።

በዞኑ ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ሃይሎች ውጭ የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይፈቀድም ግብር ሃይሉ አስታውቋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የተደራጁ ሽፍቶች በተለያዩ ጊዜያት በፈጸሙት ጥቃት ዜጎች መገደላቸውና በርካታ ንብረት መውደሙ ይታወቃል።

የዞኑን ሰላም ለማስከበር በፌዴራል መንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል የአከባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ዞኑን በማረጋጋት ላይ ይገኛል።አሁን ላይ በዞኑ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑም ተጠቁሟል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪና የግብረ ሃይሉ ማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ እንዳሉት፤ ግብርሃይሉ ከሚወስደው የህግ ማስከበር እርምጃ ጎን ለጎን እርቅና አብሮነት ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው።

በዞኑ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ያሉ ህዝባዊ የውይይቶች ጥሩ ውጤት የተገኘባቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በተከሰተው የጸጥታ ችግር ተደናግረውና በሽፍታው ተገደው ወደ ጫካ ገብተው ከነበሩ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት መካከል በርካታ እናቶች ሜዳ ላይ ለመውለድ ተገደዋል፤ ህጻናትም በችግር ውስጥ ይገኛሉ ብለዋል አቶ ተስፋዬ።

ሆኖም ግብረ ሃይሉ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ባደረገው ውይይትና የማህበረሰብ ሬዲዮ ጨምር በመጠቀም ወደየቀያቸው እንዲመለሱ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም እስካሁን ከ25 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ አባላት ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን ተናግረዋል።

ህገ-ወጥ ቡድኑ በንጹሃን ላይ በፈጸመው ዘግናኝ ድርጊት የጉሙዝም ሆነ የሌላው ማህበረሰብ ላይ ጉዳት መድረሱን ገልጸው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ህብረተሰቡ ከጥላቻና ቂም በመውጣት ሽፍታውን በጋራ መዋጋት እንዳለበት አሳስበዋል።

"የእነዚህ ሃይሎች ዋነኛ ዓላማ የህዝብ ለህዝብ ግጭትና እልቂት እንዲፈጸም መስራት መሆኑን ተገንዝበን በጋራ ልንከላከላቸው ይገባል" ብለዋል።

የግብረ ሃይሉን የጸጥታና ህግ ማስከበር ስራ የሚመሩት ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በየአከባቢው ያሉ ወንጀለኞችን ለጽጥታ አካላት አሳልፎ በመስጠት የሚጠበቅበትን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት ለመፈጸም የሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ የሚወሰደው እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በዞኑ ከተፈቀደላቸው የጸጥታ ሃይሎች ውጭ ምንም አይነት የጦር መሳሪያ ይዞ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም አሳስበዋል።

ይህን ክልከላ ተላልፎ የተገኘ ማንኛውም ግለሰብም ሆነ ቡድን ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ነው ያስጠነቀቁት።

የአካባቢውን ሰላም ለማስተበቅና ወንጀለኞችን ለመቆጣጠር ሲባል የተቀመጠው የሰዓት እላፊ ገደብም በአግባቡ መከበር እንዳለበት አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም