ስምንተኛው ሀገር አቀም የቅርጫት ኳስ ፕሪሜር ሊግ በድሬዳዋ ተጀመረ

67

ድሬዳዋ ጥር 16/2013  (ኢዜአ ) የተሻሉ ተተኪ ወጣቶችን ለብሔራዊ ቡድን ለመመልመል ያግዛል የተባለው 8ተኛው አገር አቀፍ የቅርጫት ኳስ የፕሪሚየር ሊግ ሻንፒዮና የመጀመሪያ ዙር የክለቦች ውድድር ዛሬ በድሬዳዋ ተጀመረ።

ውድድሩን ያዘጋጀው ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ቡድን በመጀመሪያ ጨዋታው የጎንደር ከተማን በተሻለ ብቃት አሸንፏል።

ለመጀመሪያ ጊዜ በድሬዳዋ ከተማ በተዘጋጀው የኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ክለቦች ሻንፒዮና ላይ አምስት የወንዶችና አራት የሴቶች ክለቦች ተካፋይ ሆነዋል።

የኮሮና መከላከያ መንገዶችንና መመሪያዎች ተግባራዊ በተተገበረበት የውድድሩ መክፈቻ ስነ-ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፈደሬሽን ሥራ አስፈጻሚ አባላትና አመራሮች ተገኝተዋል።

ውድድሩን ያስጀመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ወጣቶች ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሻኪር አህመድ እንደተናገሩት፤ በድሬዳዋ ቅርጫት ኳስን ለማሳደግና ተተኪዎችን ለማፍራት ለሚደረገው ጥረት ውድድሩ ብዙ ልምዶች የሚገኙበት ነው።

“የተሰጠን ዕድልም የዘርፉን ስፖርት በአሠራርና በአደረጃጀት ዘመናዊ መንገድ ለመከተል የጀመርነው ጎዳና ለማቃናት ያግዘናል” ያሉት ኮሚሽነሩ ተሳታፊዎች ኮሮናን የመከላከያ ዘዴዎችን ሳይዘናጉ አክብረው እንዲንቀሳቀሱ አሳስበዋል፡፡

“ሀገራችን በቅርጫት ኳስ በአፍሪካ ደረጃ የሚገባትን ቦታ እንድታገኝ መንግስት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እያገዘ ይገኛል” ያሉት ደግሞ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፈደሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ይመር ኃይሌ ናቸው፡፡

ውድድሩ ተተኪ ወጣቶችን ለብሔራዊ ቡድን ለመመልመል መድረክ በመሆን እንደሚያገለግል የገለጹት ኃላፊው ከተለያዩ የስፖርት አካዳሚዎች የመጡ ባለሙያዎች ይህን ተልኮ አንግበው በውድድሩ ላይ መገኘታቸው መልካም አጋጣሚ እንደሆነም አስረድተዋል።

በተለይ በቅርጫትኳስ ዘርፍ ታዳጊ ወጣቶች በፕሮጀክት ታቅፈው እንዲያድጉ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

“ከውድድሩ ጎን ለጎን በድሬዳዋ ለስፖርቱ የተሰጠው ልዩ ትኩረት እንዲጠናከር አስፈላጊው ሙያዊ እገዛ ይደረጋል” ብለዋል።

ለአንድ ሳምንት የሚቆየው የመጀመሪያው ዙር ውድድር ድሬዳዋ ከተኪያሄደ በኃላ በቀጣይ በባህዳር ይቀጥልና የመጨረሻው ዙርና የማሸነፊያው ውድድር አዲስ አበባ ላይ እንደሚኪያሄድ ተናግረዋል።

የአማራ መንገድና ህንጻ ዲዛይን የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ በለጠ ፀጋ የተደረገላቸው አቀባበል የሚያስደስትና ፍቅርንና አንድነትን የሚያጠናክር መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።

“ስፖርተኞቹ ከውድድሩ ባሻገር በአንድ ስፍራ በአንድነት መገናኘታቸው የእርስ በርስ ግንኙነትን በማጠናከር የሰላምና የአንድነት ጉዳይ ላይ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት ያግዛቸዋል” ብለዋል።

በኮሮና ወረርሽኝ ሣቢያ ከአንድ ስፍራ ወደሌላ ስፍራ ተዘዋውሮ መጫወት መቅረቱና ሁሉም በአንድ ቦታ መሰባሰቡ የየአካባቢውን ባህልና ወግ ለማወቅና ከተሻለው ቡድንና ተጫዋቾች ጥሩ ልምድ ለመቅሰም ያግዛል” ያለው ደግሞ የድሬዳዋ ቅርጫት ኳስ ቡድን ተጫዋቾች ሬት ፓቱም ነው።

ዛሬ ማለዳ በተካሄደው የመክፈቻ ጨዋታ ሃዋሳ ከተማ የሴቶች ቡድን የአማራ መንገድና ህንፃ ዲዛይን ቡድን 77 ለ 28 ቅርጫት አሸንፏል፡፡

ተመልካቾቻችንና ስፖርተኞችን ባዝናናውና ብርቱ ፉክክር በታየበት ሃዋሳ ከተማ የወንዶች ቡድን የወልቂጤ አቻውን 47 ለ42 ቅርጫት ማሸነፍ ችሏል፡፡

ጅማ ከተማ የሴቶች ቡድን በውድድር ባለመቅረቡ ለተጋጣሚው ወልቂጤ ከተማ 20 ቅርጫት ተመዝግቦለታል፡፡

ማምሻውን በተካሄደው ውድድር ደግሞ የድሬዳዋ ከተማ የወንዶች ቡድን የጎንደር አቻውን በተሻለ ብቃትና ብልጫ 75 ለ 38 ቅርጫት በማሸነፍ የመጀመሪያ ድሉን ተቀናጅቷል፡፡

ውድድሩ ነገም እንደሚቀጥል ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም