ተመራቂዎች ከሙስናና ከብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ህዝብን ልታገለግሉ ይገባል-- አቶ አገኘሁ ተሻገር

74

ደብረ ብርሃን ጥር16/2013 (ኢዜአ)ተመራቂ ተማሪዎች ከሙስናና ከብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ያስተማራቸውን ህብረተሰብ እንዲያገለግሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር አሳሰቡ።

ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያሰለጠናቸውን 3 ሺህ 344 ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የእለቱ ክብር እንግዳ አቶ አገኘሁ ተሻገር "ካለው  ላይ ቀንሶ ያስተማራችሁን ህዝብ ከሙስናና ከብልሹ አሰራር በፀዳ መልኩ ካለአንዳች አድሎ በቅንነት ልታገለግሉ የገባል" ሲሉ ለተመራቂዎች የማሳሰቢያ መልእክት አስተላልፈዋል።

"ሀገራችሁን ከውስጥና ከውጭ ጠላቶች በመጠበቅ በጥናትና ምርምር የተደገፈ ሞጋች ማህበረሰብ ለመፍጠር መትጋት ይገባችኋል" ሲሉም አስገንዘበዋል።

 "ተመራቂዎች ደስታችሁ ዘላቂ እንዲሆን እራሳችሁንና ቤተሰቦቻችሁን ከኮቪድ 19 ወረርሽኝ መጠበቅ አለባችሁ" ብለዋል ርእሰ መሰተዳደሩ በመልእክታቸው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ንጉስ ታደሰ በወቅቱ እንደገለጹት በመጀመሪያ፣  በሁለተኛና በሦስተኛ ዲግሪ የተሰጣቸውን ስልጠና አጠናቀው ለምረቃ ከበቁ ተማሪዎች መካከል 1 ሺህ 330 ዎቹ ሴቶች ናቸው።

የእለቱ ተመራቂ ተማሪዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በመማር  ማስተማር ሂደት ላይ  ያሳደረውን ጫና በመቋቋም ትምህርታቸውን ሊያጠናቅቁ መብቃታቸውን ተናግረዋል።

የደብረ ብርሃን ዩንቨርስቲ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአሁኑ ትውልድ የመልካም ምግባር አረአያ ናቸው ላለቸው ለመጋቢ ተክለፃድቅ ሸዋረጋ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ ሰጥቷል።

በተፈጥሮ ሳይንስ የትምህርት ክፍል 3 ነጥብ 99 በማምጣት በማእረግ የተመረቀው ገብረማሪያም አዳነ  "ኮሮና  በትምህርታችን ላይ ጫና ቢያሳድርም ተቋቁመን መመረቅ በመቻላችን ተደስተናል" ብሏል።

በተማረበት የትምህርት ዘርፍ በአፈርና ውሃ ጥበቃ አርሶ አደሩን በአግባቡ በማገልግል የአካባቢ አየር ንብረት ለውጥን ለከመላከል እንደሚሰራ አስታውቅል።

በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ የተቋማት የስራ ሀላፊዎችና የተመራቂ ቤተሰቦች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም