በመከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት እንዲደርስ የመሩና ያቀናጁ የሕወሃት አመራሮች ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂ ናቸው-የቀድሞ የሕወሃት ታጣቂዎች

101

ጥር 16/2013 (ኢዜአ) በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት እንዲደርስ የመሩና ያቀናጁ የሕወሃት አመራሮች ለዚህ ሁሉ ጥፋት ተጠያቂ መሆናቸውን የትግራይ የቀድሞ ልዩ ሃይል፣ ፖሊስና ሚኒሻዎች ተናገሩ። የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ታሪክ ተፈፅሞ የማያውቅ ክህደት መፈፀሙንም ገልጸዋል።

የሕወሃት ጁንታ ለእኩይ ተልዕኮ ቢያሰልፋቸውም "መከላከያ ሰራዊትን አንወጋም" በሚል እጃቸውን ለሰራዊቱ ከሰጡ የልዩ ሃይል ፖሊስ አባላት መካከል አብርኸት መውጫና ትዝታ ካሳሁን ይገኙበታል።

በቁጥጥር ስር በዋሉበት ወቅት የሕወሃት ጽንፈኛ ቡድን የደሃ ልጆችንና እድሜያቸው ለውጊያ ያልደረሱ ታዳጊዎችን በማስገደድ ለውጊያ ማሰለፉን በማውገዝ የጁንታውን እኩይ አላማ ማውገዛቸውም ይታወቃል።

ወጣቶቹ ላለፉት ሁለት ወራት በብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ድጋፍ በአዋሽ አርባ በሚገኘው የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል የተሃድሶ ስልጠና ላይ ይገኘሉ።

አበርኸት እና ትዝታም ስልጠናው ሲሳቸው ከነበሩ ከ750 በላይ የቀድሞ የሕወሃት ልዩ ሃይል፣ ፖሊስና ሚሊሻዎች መካከል ይገኙበታል።

በተሃድሶ ስልጠና ቆይታቸው አስፈላጊው ግብዓት እንደተሟላላቸውና በመከላከያ ሰራዊት እንክብካቤ ሲደረግላቸው መቆየቱንም ያስረዳሉ።

ከአብርኸትና ትዝታ በተጨማሪ ከመከላከያ ተሰናብቶ በክልሉ ልዩ ሃይል አባል የነበረው ተስፋዬ ጥላሁን፣ እንዲሁም የሚሊሻ አባላት የነበሩት አቶ ሞላ ነጋልኝና አቶ ይብራ ሃይለስላሴም አያያዛቸው መልካም አንደሆነ ገልጸዋል።

በተሃድሶ ስልጠና ላይ የቆዩት ታጣቂዎቹ በሕወሃት ሰዎች መጠቀሚያ መሆናቸው እንዳስቆጫቸው ገልፀው፤ በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ የተፈጸመው ጥቃትም ታሪካዊ ስህተት መሆኑን አንስተዋል።

ለዚህ ድርጊት የሕወሃት ፅንፈኛ ቡድን አመራሮች ጠንሳሽና አስፈፃሚዎች እንደነበሩ አስታውሰው ለደረሰው ጥፋት ሁሉ ዋነኛ ተጠያቂዎች ናቸው ብለዋል።

ድርጊቱ የትግራይ ህዝብ ፍላጎትና ምክር ሳይሆን የድርጊቱ ጠንሳሽና አስፈጻሚ በንጹሃን ደም ስልጣን ላይ መቆየት የሚፈልገው የሕውሃት ቡንድ ሴራ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

መንግስት አሁን ላይ በሕወሃት ቡድን ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ተገቢ መሆኑን አንስተው በቁጥጥር ስር የዋሉ የድርጊቱ አስፈጻሚዎች በሕግ ተጠያቂ መሆን ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ከተሃድሶሰ ስልጠናው በኋላ ወደ ቀደመ ሰላማዊ ኑሮ በመመለስ ከኢትዮጵያዊያን ጋር በየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ ተዘዋውረው መስራትና ሕይወታቸውን መምራት እንደሚፈለጉም ተናግረዋለ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም