ወጣቱ ለሀገሩ ብልጽግና በምክንያታዊ አስተሳሰብ የተመሰረተ ትግል ሊያደርግ እንደሚገባ ተገለጸ

59

ደሴ፣ ወለዲያና ደብረ ብርሃን ጥር 16/2013 ( ኢዜአ ) ወጣቱ ባካሄደው ጠንካራ ትግል አገራዊ ለውጥ እንዲመጣ እንዳደረገ ሁሉ የተገኘውን ድል ለማስቀጠልም በስሜት ሳይሆን በምክንያታዊነት መታገል እንደሚጠበቅበት ተገለፀ።

"ምክንያታዊ ወጣት ለሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ቃል በደሴ፣ ኮምቦልቻና ወልዲያ ከተሞች ውይይት ተካሄደ።

በብልጽግና ፓርቲ የወጣቶች ሊግ ፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይልማ ተረፈ እንደገለጹት በተለያየ ጊዜ ለሚመጣው ለውጥና ድል የወጣቱ ድርሻ ከፍተኛ ነው።

በሃገራችን በመጣው ለውጥም የወጣቱ ትግል ላቅ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ለውጥ ግቡን እንዲመታም ተስፋ ሳይቆርቱ የበለጠ ትግል ማድረግ ይገባል።

“ወጣቱም ከስሜት በመውጣት ትክክለኛ ታሪኩን ከአባቶች ተረድቶ የበፊቱን የአንድነት፤ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን ማስቀጠል ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

የደቡብ ወሎ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮነን በበኩላቸው “ወጣቱ ለማንኛውም ጉዳይ ሰከን ብሎና ተረጋግቶ ለሀገረ መንግስቱ ግንባታ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል”ብለዋል።

“ከስሜት ተላቆ ምክንያታዊ በመሆን ለልማት፤ ለሰላምና ለብሔራዊ መግባባትም መስራት ይጠበቅበታል” ብለዋል፡፡

ብልጽግና ፓርቲ ወጣቱን ፍትሃዊ የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ተጠቃሚ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ አዳዲስ ወጣት አመራሮች ወደ ፊት እየመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።

ወጣቱን ግንባር ቀደም አድርጎ ያላሳተፈ ልማት ዘላቂነት የለውም ያለችው በኮምቦልቻ መድረክ ተሳታፊ የሆነችው ወጣት ጀሚላ ሃሰን ናት።

መንግስት ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነቱን በተግባር ማሳየት እንዳለበት ጠቁማ ለሀገር አንድነትና ሰላም በቅንጅት በመስራት የድርሻዋን እንድምትወጣ ገልጻለች።

በወልዲያ ከተማ በተካሔደው መድረክ ላይ ደግሞ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ወልደትንሣኤ መኮንን እንዳሉት ወጣቱ በትግሉ ሀገራዊ ለውጥ እንዳመጣ ሁሉ የተገኘውን ድል ለማስቀጠል በምክንያታዊነት መታገል ይገባል። 

ሀገር ሰላም የሚሆነውና ልማት የሚፋጠነው ወጣቱ ከመንግስት ጎን ተሰልፎ በጋራ ሲሰራ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ወጣት አህመድ ደጉ በሰጠው አስተያየት መድረኩ ለወጣቱ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሶ፤ በተሳሳቱ ትርክቶች ፣ በህገ መንግስቱና መሰል አጀንዳዎች የጋራ መግባባት እንዲመጣ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ መሰራት ይገባል። 

“ወጣቱ በሀገራዊ አንድነት ንቁ ተሳታፊና በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆን መንግስት አበክሮ ሊሰራ ይገባል” ያለው ደግሞ የውይይቱ ተሳታፊ ወጣት ዋሲሁን ጫኔ ነው።

በደብረብርሃን ከተማ በተካሔደው ውይይት ላይ ደግሞ የሰሜን ሸዋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታደሰ ገብረፃድቅ “ሸዋ ከመካከለኛው ክፍለ ዘመን ለሀገረ መንግስትና ለብሄረ መንግስት ግንባታ የነበረው ተሳትፎ ከፍተኛ ነበረ” ብለዋል።

“ይሁን እንጂ ባሳለፍነው ግማሽ ምእተ አመት ታሪክ ውስጥ የአማራ ተወላጆች ከሌሎች እህትና ወድሞቹ ጋር ተስማምቶ እንዳይኖር በተሰራ የሃሰት ትርክት ለስደት፣ ለመፈናቀልና ለሞት እየተዳረገ ይገኛል”ብለዋል።

ይህ የተሳሳተ ትርክት እንዲስተካከልና ዜጎችን ከሞት ለመታደግ ችግሩን በሰከነና በምክንያት በማቅረብ አንዲፈታ መታገል እንደሚገባም አስረድተዋል።

በሃገሪቱ የተጀመረው ለውጥ ግቡን እንዲመታ የብልፅግና ጉዞው እንዲሳካ ወጣቱ የድርሻቸውን መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።

ጠያቂና ምክንያታዊ ወጣት ለመፍጠር እየተደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን የገለፀው ደግሞ በውይይቱ የተሳተፈው መምህር አየለ ግዛቸው ነው።

ትላንት በሶስቱ ከተሞች በተካደው ሐካየምክንያታዊ ወጣቶች ግንባታ የውይይት መድረ ላይ ከ አንድ ሺህ 700በላይ  ወጣቶች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም