ከ750 በላይ የቀድሞ የትግራይ ልዩ ሃይል፣ ፖሊስና ሚሊሻ አባላት ከተሐድሶ ስልጠና በኋላ ወደ አካባቢያቸው ሊመለሱ ነው

99

ጥር 16/2013(ኢዜአ) ከ750 በላይ የቀድሞ የትግራይ ክልል ልዩ ሃይል፣ ህዝባዊ ፖሊስና ሚሊሻ አባላት ከተሐድሶ ስልጠና በኋላ ወደየ አካባቢያቸው ተመልሰው መደበኛ ህይወታቸውን ይመራሉ።

የሕወሃት ቡድን በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ በተደረገው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት በርካታ የቀድሞ የሕወሃት ታጣቂዎች ለመከላከያ ሰራዊት እጃቸውን ሰጥተዋል።

ከነዚህም መካከል በአፋር ክልል አዋሽ አርባ በሚገኘው የደቡብ ዕዝ ማሰልጠኛ ማዕከል 764 የቀድሞ የትግራይ ልዩ ሃይል፣ ፖሊስና ሚሊሻ አባላት በአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ድጋፍ የተሃድሶ ስልጠና ሲሰጣቸው ቆይቷል።

የኮሚሽኑ ጽህፈት ቤት ሃላፊና የተሃድሶ ስልጠናው አስተባባሪ አቶ ዘሪሁን ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ አብዛኛው ሰልጣኞች ከግብርና ስራ ላይ ተገደው ወደ ውጊያ የተሰማሩ አርሶአደሮች እንደሆኑ ገልጸዋል።

ከፖሊስና ሚሊሻ አባላቱ በርካቶቹ በፅንፈኛው የሕወሃት ቡድን ጠባብነትና ተገፊነት እኩይ አስተሳስቦች ሰለባ በመሆናቸው የተሃድሶ ስልጠና ማስፈለጉን ገልጸዋል።

በዚህም ወጣቶች የአገራዊ ለውጡን ምንነትና የህግ ማስከበር ሂደት የአቅም ግንባታና የአስተሳስብ ለውጥ ላይ ስልጠናዎች እየተሰጡ መሆኑን አቶ ዘሪሁን ተናግረዋል።

የብሔራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን እጅ ከሰጡበት ጊዜ ጀምሮ ከሎጀስቲክስ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ አድርጎ በአዋሽ አርባ የተሐድሶ ስልጠና ሲወስዱ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም ወደየ አካባቢያቸው ተመልሰው ከህብረተሰቡ ጋር ተቀላቅለው መደበኛ ህይወታቸውን ይመራሉ ብለዋል።

ሰልጣኞቹ ስልጠናውን ሲያጠናቅቁ የተለየ ሁኔታ ጥፋት የፈጸሙ ካልሆኑ በስተቀር ቀሪዎቹ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱና በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲደገፉ ይደረጋል ነው ያሉት።

ከመጀመሪያው ምዕራፍ ስልጠና በተጨማሪ ሌሎች ተጨማሪ ስልጠናዎች ተሰጥተው በቀጣይ ሶስት ሳምንት ተጠናቆ አባላቱ ወደየ አካባቢያቸው ይመለሳሉ።

የትይግራይ ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነብዩ ስሁል በበኩላቸው እየተሰጠ ያለው ስልጠና የአባላቱን አቅም ለመገንባት፣ ህዝብና አገራቸውን የሚክሱበትና ራሳቸውን የሚለውጡበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ስልጠናው በጥሩ ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸው፤ ሲጠናቀቅም በቅርቡ በነጻነት ተንቀሳቅሰው ህይወታቸውን መምራት ይጀምራሉ ብለዋል።

የጋራ አስተሳሰብ በመያዝ የአገርን ብልጽግና ለማረጋገጥ፤ እንዲህ አይነት የተሀድሶ ስልጠናውን ላላገኙት ይሰጣልም ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም