ከስደት ተመላሾችን የማደራጀትና የስራ እድል የመፍጠር ተግባር በሚፈለገው ልክ ውጤታማ አለመሆኑ ተነገረ

71

ደሴ፤ ጥር 16 /2013(ኢዜአ) በአማራ ክልል ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማደራጀትና የስራ እድል ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት በቅንጅት መጓደል ምክንያት በሚፈለገው ልክ ውጤታማ ሊሆን አለመቻሉ ተገለፀ። 

የአማራ ክልል ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዝ ልማት ቢሮ በጉዳዩ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በኮምቦልቻ ከተማ ውይይት አካሂዷል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ባንችይርጋ መለሰ እንደገለጹት በክልሉ በህጋዊና በህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ ከሄዱ በኋላ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው ስራ አጥ የሆኑ ዜጎች ቁጥር በርካታ ነው።

ከስደት ተመላሾቹ በውጭ ሃገራት በቆዩባቸው ጊዜያት በሚፈጠርባቸው ጫና አብዛኞቹ ስነ ልቦናዊ ችግር ያለባቸው መሆናቸውን ተናግረው፤ "ወደ ሃገራቸው ከመጡ በኋላም ለቤተሰብ ጥገኛ እየሆኑ ጭንቀት ውስጥ እየወደቁ ይገኛሉ" ብለዋል።

ከስደት ተመላሾችን መልሶ ለማቋቋም በተለያዩ የስራ ዘርፎች የስራ እድል ለመፍጠር የክልሉ መንግስት ጥረት እያደረገ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

"ይሁንና በበጀት ዓመቱ ለ13 ሺህ 300 የስደት ተመላሾች የስራ እድል ለመፍጠር ቢታቀድም ባለፉት ስድስት ወራት የስራ እድል የተፈጠረላቸው 1 ሺህ 700 ብቻ ናቸው" ያሉት ምክትል ሃላፊዋ፤ ወደ ስራ ለማሰማራት በሚደረገው ጥረት በባለድርሻ አካላት ቅንጅት መጓደል በሚፈለገው ልክ ውጤታማ መሆን እንዳልተቻለ አብራርተዋል።

ችግሩን ለመፍታት መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋምትን ጭምር በማካተት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አመልክተዋል።

በስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ጉዳይ ኤጀንሲ የስደት ተመላሾች መልሶ ማቋቋም ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስተባባሪ አቶ ምኞት ደራራ በበኩላቸው ከስደት ተመላሾች ቁጥር ከጊዜ  ወደ ጊዜ እያሻቀበ መሆኑን ተናግረዋል።

ከስደት ተመላሾቹን መልሶ ለማቋቋም ችግሩ ጎልቶ በታየባቸው አምስት ክልሎችና አንድ ከተማ አስተዳደር ኤጀንሲው እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"በርካቶች ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ጫና እንዲያገግሙና እንዲረጋጉ በባለሙያ የታገዘ ስልጠና በመስጠት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ እየተደረገ ይገኛል" ብለዋል።

በህጋዊና በህገ ወጥ መንገድ ተሰደው ለችግር የተጋለጡ ዜጎች ወደ ሀገር ቤት ሲመለሱ የስራ እድል በመፍጠር በኩል በቅንጅት ክፍተት ሰፊ ችግር እንዳለ ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፈታት  የሚመለከታቸው ተቋማት ተገቢውን አገዛ ሊያደርጉ እንደሚገባም ነው የገለጹት። 

በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የፍልሰት ብሔራዊ ትብብር ጥምረት ጽህፈት ቤት አቃቤ ህግ አቶ እያሱ ቀለሜ በበኩላቸው የስደት ተመላሾችን ቁጥር ለመቀነስ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ላይ እየተሰራመሆኑን ተናግረዋል።

ችግሩ ውስብስብና አስቸጋሪ ቢሆንም አላሰራ ያሉ የህግ ማዕቀፎችን በማሻሻል ህገ ወጥ ደላሎች ላይ የማያዳግም እርምጃ ለመውሰድ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል። 

በተለያዩ ሀገራት የሚሞቱ፣ የሚደፈሩና ለስቃይ የሚዳረጉ ዜጎችን ለመታደግ ከአጎራባች ሀገሮች ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑንም የገለጹት አቶ እያሱ፤ በወንጀል የሚጠረጠሩ ተላልፈው  እንዲሰጡና ምስክር እንዲሆኑም እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ በሚችለው አቅም ለስደት ተመላሾች የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የሸዋሮቢት ከተማ ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዝ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘነበ ተክሌ ናቸው፡፡

በህጋዊና ህገ ወጥ መንገድ ወደ ውጭ የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ ለሚመለሱት ሁሉ የስራ እድል መፍጠር እንዳልተቻለም ገልጸዋል፡፡

ስራ ማማረጥና የመሰረተ ልማት ችግር በዘርፉ መሰናክል መሆናቸውን ጠቁመው፤ ችግሩን ለመፍታት ከዞንና ከክልሎች እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በወይይቱ ከፌደራል፣ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ አመራሮች ፣ አጋር አካላትና ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም