በመተከል ዞን ጠላትን ከህዝቡ በመነጠል አስካሁን የተከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑን የተቋቋመው ግብረሃይል አስታወቀ

92

ጥር 16/2013 (ኢዜአ) በመተከል ዞን ጠላትን ከህዝቡ በመነጠል አስካሁን የተከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑን በመንግስት የተቋቋመው የተቀናጀ ግብረ ሃይል አስታወቀ።

በዞኑ ተፈጥሮ በነበረው ችግር ጫካ ገብተው የነበሩ ከ15 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ ተወላጆችም ወደ ቀያቸው መመለሳቸው ተገልጿል።

በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ አካባቢውን ከሽፍታው ቡድን ነጻ በማድረግ ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው መመለስ የሚያስችል ስራ በግብረ ሃይሉ እየተከናወነ ይገኛል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን፣ የገቢዎች ሚኒስትር ላቀ አያሌው፣ በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ተስፋዬ በልጅጌ፣ የመተከል የተቀናጀ ግብረ ሃይል አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል አስራት ዴኔሮ፤ አርቲስት ታማኝ በየነና ሌሎችም ባለስልጣናት በቻግኒ - ራንች የተጠለሉ ተፈናቃዮችን ጎብኝተዋል።

የመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረ ሃይል መሪ ሌተናል ጀኔራል አስራት ዴኔሮ፤ ታጣቂውን ሃይል ከህዝቡ በመነጠል አስካሁን የተከናወነው ስራ ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በህብረተሰቡ ትብብር በዳንጉር ወረዳ ብቻ ከሰባት ቀበሌዎች 8 ሺህ የጉሙዝ ተወላጆች ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል ብለዋል።

በዞኑ ደግሞ እስካሁን ከ15 ሺህ በላይ የጉሙዝ ማህበረሰብ ተወላጆች ችግሩን ሸሽተው ከገቡበት ጫካ ወጥተው ወደ መኖሪያቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው በበኩላቸው መንግስት በታጣቂ ሃይሉ ላይ እየወሰደ ያለውን እርምጃ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ህዝቡ የደርሻውን ሃላፊነት መወጣት አለበት ብለዋል።

ወንጀለኞቹን ወደ ህግ በማቅረብ ተጠያቂ ለማድርግም ህብረተሰቡ ከቁጭትና ትካዜ ወጥቶ ለመንግስት አጋልጦ መስጠትና ታጥቆ የጸጥታ ሃይሉን ማገዝ አለበት ነው ያሉት።

ሌተናል ጀነራል አስራት በንግግራቸው ከሁሉም ማህበረሰብ የተውጣጣ ሚሊሻ አሰልጥኖ ለማስታጠቅ በየቀበሌዎች የግለሰቦችል ዝርዝር መለየቱን ገልጸዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ አቶ አስፋዬ በልጅጌ፤ ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ተመልምለው ስልጠና የሚወስዱ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ ወደመኖሪያ ቀያቸው ሲመለሱ ከቀሪው ህብረተሰብ ጋር በመቀላቀል የአካባቢያቸውን ሰላም ማስጠበቅ እንዲችሉ ስራውን ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መንግስት እየሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቹ አርቲስት ታማኝ በየነ ባስተላለፈው መልእክትም ተፈናቃዮች የደረሰባቸውን ችግር ተቋቁመው የበደሏቸውን ቡድኖች ማሸነፍ የሚችሉበትን ስነ ልቦና መገንባት እንዳለባቸው ገልጿል።

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንም ተፈናቃዮችን ይደግፋሉ፣ የተፈናቃዮች ድምጽ በመሆን ይበልጥ ትኩረት እንዲሰጠው የሚጠይቁ መሆኑን አረጋግጧል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ፤ ክልሉ ለተፈናቃዮች ሰብዓዊ ድጋፍ በማድረግም ሆነ በዘላቂነት በማቋቋም ከፌደራል መንግስቱ ጋር በጋራ እንደሚቆም አረጋግጠዋል።

ከእለት ሰብዓዊ እርዳታ ጋር በተያያዘ ተፈናቃዮች እስካሁን በቂ የምግብ አቅርቦት እንደሌለ፤ ልብስም እንደሌላቸው አንስተዋል። ለተፈናቃዮች የእለት ደራሽ እርዳታውን የሚያከፋፍለው ኮሚቴም እስካሁን ልብስ እንዳልተሰጣቸው አምኗል።

የገቢዎች ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው መንግስት ከ24 ቀን በፊት ያመጣው ልብስ እስካሁን አለመከፋፈሉ አግባብ አይደለም ብለዋል።

መንግስት የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ዜጎች በፍጠነት እንዲደርሳቸው የላከውን ሰብዓዊ እርዳታ መጋዘን ውስጥ አሽጎ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም፤ ራሳችንንም ማየት አለብን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም