በኢትዮጵያ 40 በመቶ ዜጎች ከባድና ለመፍታት የሚያስቸግሩ የሕግ ጉዳዮች ይገጥሟቸዋል – ጠቅላይ ፍርድ ቤት

1549

አዲስ አበባ፣ ጥር 15 ቀን 2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ 40 በመቶ የሚሆኑ ዜጎች በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ከባድና ለመፍታት አስቸጋሪ የሆኑ የሕግ ጉዳዮች እንደሚገጥሟቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ገለጹ።

“የፍትህ ፍላጎቶችና የመሟላታቸው ሁኔታ በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ ትኩረቱን በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትህ ስርዓት ላይ ያደረገ ጥናታዊ ጽሁፍ ዛሬ ውይይት ተደርጎበታል።

በውይይት መድረኩ ወይዘሮ መዓዛ በአገሪቷ በአራት ዓመት እንድ ጊዜ ከሕግ ጋር የተገናኘ ችግር የሚያጋጥማቸው ዜጎች ቁጥር ቀላል የሚባል እንዳልሆነ ተናግረው፤ ፍትህ የማግኘት መብትን ለማሟላት የፍርድ ቤቶችን አገልግሎት ይበልጥ ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ይህን የዜጎች የፍትህ ጥያቄ በተሟላ ሁኔታ ለመመለስ መደበኛ የፍትህ አሰጣጥ ስርዓቱ ብቻ በቂ እንዳልሆነም አመልክተዋል።

በፍርድ ቤቶች ከሚሰጠው አገልግሎት በተጨማሪ መደበኛ ያልሆኑና አማራጭ የሙግት መፍቻ መንገዶችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ነው ፕሬዚዳንቷ የገለፁት።

ከዚህ አንጻር በከባድ ወንጀል ተከሰው ራሳቸው ጠበቃ ቀጥረው መከራከር ለማይችሉ ተከሳሾች በነጻ ተከላካይ ጠበቃ አግኝተው መብታቸውን የሚያረጋግጡበትን ሁኔታ ለመፍጠር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

አቅመ ደካማና ጥቃት የተፈጸመባቸው ሴቶች የሚጠይቁትን ድጋፍ በማሟላት ፍትህ የማግኘት መብታቸው እንዳይጓደል የሚረዱ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም ወይዘሮ መዓዛ ተናግረዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ በበኩላቸው ጥናቱ ለአንድ ዓመት በስድስት ክልሎች ላይ ትኩረት አድርጎ መካሄዱንና ከ5 ሺህ 400 በላይ ሰዎች እንደተሳፉበት ገልፀዋል።

ጥናቱ የአገሪቷ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ያለበትን ደረጃና በአገልግሎቱና በፍላጎቱ መካከል ያለውን ልዩነት ማሳየቱንም አክለዋል።

ይህም የፍትህ ስርዓቱን በሚመለከት በጥናት ላይ የተመሰረተ ፖሊሲ ለመቅረጽና አሁን ካለው የፍትህ አሰጣጥ የተሻሉ ሃሳቦችን ለማፍለቅ እንደሚረዳ ዶክተር ጌዲዮን አስረድተዋል።

የፌዴራል የፍትህና የሕግ ምርምርና ስልጠና ኢንስቲትዩት የጥናትና ምርምር ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ማዳ ጥናቱ ኅብረተሰቡን ያማከለና የተስተካከለ የፍትህ ስርዓት ለመቅረጽ እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በጥናቱ በኢትዮጵያ በየዓመቱ 7 ነጥብ 4 ሚሊዮን ተጽዕኖ የሚፈጥሩ የሕግ ጉዳዮች እንደሚከሰቱ አመላክቷል።