ዘ ኢኮኖሚስት’ ጋዜጣ ያወጣው የኢትዮጵያ መንግስት ‘ረሃብን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል’ የሚለው ዘገባ የተሳሳተ መሆኑ ተገለጸ

93

ጥር 14/2013 ( ኢዜአ) የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መረጃ ማጣሪያ ‘Letter to the The Economist Newspaper’ በሚል ባወጣው መረጃ ላይ እንዳመላከተው፤ የኢትዮጵያ መንግስት ‘ረሃብን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል’ መባሉ የሚወገዝ ነው።

የኢትዮጵያ መንግስትንም የማይገልጽ እንደሆነ አስገንዝቧል።

በጋዜጣው የወጣው አርቲክል ተቀባይነት የሌለው ክስ መሆኑን አመልክቶ፤ ባለፈው ወር የኢትዮጵያ መንግስት 31 ሺህ ሜትሪክ ቶን ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች እና የመድሃኒት ግብዓቶችን ለትግራይ ማቅረቡን አስታውሷል።

በተጨማሪም መንግስት አስፈላጊውን የጸጥታ ፕሮቶኮል በማሟላት የዜጎችን ደህንነት መጠበቁን፣ ክልሉን የማረጋጋት ስራ መስራቱንና ቀሪ ወንጀለኞችን የመያዝ ዘመቻ እያካሄደ እንደሆነ አመልክቷል።

ይህ ሆኖ ሳለ በጋዜጣው የወጣው አርቲክል የኢትዮጵያ መንግስትን ጥረት የማደፋፈንና ዋጋ የማሳጣት ዝንባሌ ያለው ከመሆን አልፎ ‘መንግስት ብቁ አይደለም’ የሚል ዘለፋ እንደሆነ የመረጃ ማጣሪያ ገልጿል።

የአገር መከላከያ ሰራዊት የህግ ማስከበር ዘመቻውን ልዩ የሆነ ብቃት በማሳየት እንደተወጣው ገልጾ፤ በትግራይ ክልል የጸጥታ ማስከበር ስራዎችን ከመስራት ጎን ለጎን መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ እንደሆነ አመልክቷል።

በክልሉ የተለያዩ አገልግሎቶች በተሟላ መልኩ እንዲመለሱ የተለያዩ ተቋማት እየሰሩ እንደሆነ አመልክቶ፤ የህወሃት ቡድን ቴሌኮም፣ ትራንስፖርት፣ ባንክን ጨምሮ የመንግስትና የግል መሰረተ ልማቶችን የማውደም ተግባር መፈጸሙ የሚታወቅ መሆኑን ጠቅሷል።

መሰረተ ልማቶቹን መልሶ መገንባት ጊዜ እንደሚፈልግ በመግለጽ የተሳሳተ መረጃ በጋዜጣው መውጣቱ ስህተት መሆኑን ገልጿል።

ከሰብዓዊ መብት መከበር ጎን ለጎን ሰላምና የህግ የበላይነት መከበርን የኢትዮጵያ ህዝብ እንደሚፈልግ ያስረገጠው መረጃ ማጣሪያ፤ የጋዜጣው አርቲክል የህወሃትን ስልታዊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ታሪክ ወደጎን የተወና የካደ እንደሆነም ጠቅሷል።

ህወሃት ባለፉት ሶስት አስርታት በኢትዮጵያ ለተፈጸሙ አለመረጋጋቶች፣ ሽብርና የጅምላ ግድያ ዋናው ስፖንሰር እንደነበር አመልክቷል።

ይህንን ቡድን የፍትህ ፍላጎት ያለው የኢትዮጵያ ህዝብ በተባበረ ጥረት እንዳስወገደውም ገልጿል።

የጋዜጣው አርቲክል ዋነኛ ስህተት አርቆ ማየት የተሳነው መሆኑ እንደሆነ የገለጸው መረጃ ማጣራት፤ “ያለፉት ሁለት ዓመታት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ህመም የነበሩ ናቸው፤ ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግስት በአሁኑ ወቅት ትክክለኛውን አቅጣጫ መያዙን ያምናል” ብሏል።

መከራን በማጉላትና ክስን በማስጮህ እንዲሁም ካለፈው የመንግስት አስተዳደር ጋር ለውጡን ማነጻጸር የውድቀት ያህል መሆኑን መረጃ ማጣሪያ አስገንዝቧል።

ኢትዮጵያውያን ያለፈው ታሪክ እንዲደገም እንደማይፈልጉ ገልጾ፤ የኢትዮጵያ መንግስት እንደ ህወሃት ዓይነቶቹ አዲሱን ምዕራፍ እንዲጠልፉ የማይፈቅድ መሆኑን በጽኑ አስገንዝቧል።

መንግስት ታሪካዊ የሆነ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ጉዳዮች የለውጥ ሂደት ውስጥ መሆኑን አመልክቶ፤ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ዘመን ለመግባት የምታደርገውን ጥረት እውን ለማድረግ በትግራይ ክልል ያካሄደችው የህግ ማስከበር ዘመቻ ዋጋ ቢያስከፍልም የግድ አስፈላጊ ርምጃና ትክክለኛ አቅጣጫ እንደሆነ ገልጿል።

በመሆኑም ‘ዘ ኢኮኖሚስት’ የአፍሪካን መሪዎች ወይ ሴጣን ወይ ደግሞ ብቁ አይደሉም በማለት ያሰፈረውን ጽሁፍ የሚያሳፍር መሆኑን በመግለጽ በጽኑ አውግዞታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም