የባህር ዳር ከተማን የቱሩዝም መስህብነት ለማጎልበት የሚያግዝ የታንኳ ውድድርና የጀልባ ትርኢት ተካሄደ

1698

ባህርዳር ፤ጥር 15/2013( ኢዜአ) የባህርዳር ከተማን የቱሩዝም መስህብነት ለማጎልበት የሚያግዝ በጣና ሃይቅ ላይ ዓመታዊ የታንኳ ውድድርና የጀልባ ትርኢት ትናንት ማምሻውን ተካሄደ። 

የከተማዋ አስተዳደር  ምክትል ከንቲባ አቶ ባየ አለባቸው በወቅቱ እንደገለጹት የታንኳ ውድድርና የጀልባ ትርኢቱ ዓላማ ባህርዳር በተፈጥሮ መስህቦች የተከበበች ሳቢና ማራኪ ከተማ መሆንዋን አጉልቶ ለማሳየት ነው።

ዝግጅቱ በየዓመቱ ጥር ወር እንደሚካሄድና ይህም ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ ወደ ከተማዋ የሚመጡ ቱሪስቶችን የቆይታ ጊዜ ለማራዘምና የባህርዳርን ገጽታ ለዓለም ህብረተሰብ ይበልጥ ለማስተዋወቅ በማሰብ እንደሆነም አስረድተዋል።

የአማራ ክልል በርካታ የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ቢሆንም በአግባቡ አልምቶ በመጠቀም በኩል ውስንነት እንዳለ የገለጹት የክልሉ  ባህልና ቱሪዝን ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ ናቸው

የጣና ሃይቅን የቱሪዝም መዳረሻ ማዕከል ለማድረግ የተጀመረው ጥረት እንዲጠናከርም በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

ሃይቁን የጀልባ ትርኢትና የታንኳ ውድድር ስፖርት መዳረሻ እንዲሆን በማድረግ እንደ ክልልም ሆነ እንደ ሀገር ትልቅ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ ይቻላል ያሉት ዶክተር ሙሉቀን የከተማዋ አስተዳደርም የጀመረው ሥራ ሊበረታታ የሚገባው መሆኑን ተናግረዋል።

ሁለት ኪሎ ሜትር የደርሶ መልስ  ርቀትን በሸፍነው የታንኳና የጀልባ ውድድር 55 ባለታንኳዎች የተሳተፉ ሲሆን 30 ጀልባዎች ደግሞ በጣና ሀይቅ ላይ ትርኢት አሳይተዋል።

ከአምስት ሺህ በላይ ታዳሚዎች በተገኙበት በተካሄደው የታንኳ ውድድርና የጀልባ ትርኢት ከአንደኛ እስከ ሶሰተኛ ደረጃ ለወጡ የገንዘብና ዋንጫ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

የታንኳ ውድድር መጀመሩ የሚበረታታ ቢሆንም በክለብ ታቅፎ እስካልተያዘ ድረስ ቀጣይነት ላይኖረው ይችላል ያለው ደግሞ በታንኳ ውድድር አንደኛ የወጣው ወጣት ፈንታሁን ደሳለኝ ነው።

ውድድሩን ለማጠናከርና የቱሪዝምን ፍሰቱን እንዲጨምር ለማስቻል ከተፈለገ ባለታንኳዎችን ዓመታዊ ዝግጅቱ ሲደርስ ብቻ ሳይሆን በክለብ አቅፎ መንከባከብና ማሰልጠን ይገባል ብሏል።