የዘንደሮውን ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ከወዲሁ መፍጠር ይገባል--የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት

56

ጥር 14/2013 (ኢዜአ) የዘንደሮውን ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ከወዲሁ መፍጠር እንደሚገባ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ገለጸ።

ባለፈው ዓመት የሰላም ሚኒስቴር፣ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን፣ ዴስቲኒ ኢትዮጵያና የሃሳብ ማዕድን ጨምሮ በአጠቃላይ ሰባት ድርጅቶች  "ማይንድ ኢትዮጵያ"ን በጋራ መመስረታቸው ይታወሳል።

ማይንድ ኢትዮጵያ ከሚያዘጋጃቸው ሁሉን አቀፍ የምክክር አጀንዳዎች መካከል ብሔራዊ መግባባት አንዱ ነው።

ባለፈው ሳምንትም የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ለሆኑ 38 ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በብሔራዊ መግባባት ላይ ያላቸውን ሚና አስመልክቶ የሦስት ቀናት የምክክር መድረክ አካሂዶ ነበር።

የጋራ ምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ በመድረኩ የተለያዩ አጀንዳዎች ለውይይት ቀርበው መግባባት ላይ የተደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በተለይ በአገሪቱ በዚህ ዓመት የሚካሄደውን አገራዊ ምርጫ አስመልክቶ ምርጫው ከመካሄዱ በፊት መግባባት ላይ ሊደረስባቸው የሚገቡ 10 ዋና ዋና ነጥቦች መለየታቸውን ነው የጠቆሙት።

ከእነዚህም ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችል በቂ ዝግጅት መኖር አለመኖሩን ማረጋገጥ፣ በምርጫው ተሳታፊዎችና ታዛቢዎች እንዲሁም ሌሎች የምርጫ ሂደት ጉዳዮች ላይ መግባባት መፈጠር አለበት የሚሉት ይገኙበታል።

በምርጫ አስፈጻሚነት ላይ መተማመን፣ በአገሪቱ ያለው የሰብአዊ መብቶች አከባበር ጋር በያያዘ የመንግስት ኃላፊነትና ተጠያቂነት ላይ ግልጽነት መኖር እንዲሁም አገራዊ ሰላምና ጸጥታ ሁኔታዎች ምን ይመስላሉ የሚሉትም እንዲሁ በፓርቲዎቹ መግባባት ላይ እንዲደረስ የተለዩ ናቸው።

አቶ ግርማ እንዳሉት ከምርጫው ጋር የሚገናኝ የብሔረሰብ ማንነት ጥያቄ እና የምርጫ ክልል ተያያዥነት ያሉ ጉዳዮች በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ችግር እንዳይፈጥሩ አስቀድሞ ማጥራት እንደሚገባም ከስምምነት ተደርሷል።

በምርጫው ውጤት ሊነሱ ስለሚችሉ ቀውሶች ተጠያቂነትም በተመለከተ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የጸጥታ አካላት ገለልተኝነት እና የመገናኛ ብዙሃን ሚዛናዊነትን አስመልክቶም ሁሉንም እኩል ሊያስተናግዱ በሚችሉበት ሁኔታ ላይ እንዲሰሩ ነው በፓርቲዎቹ ስምምነት ላይ የተደረሰው።

ምርጫውን ለማካሄድ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ከወዲሁ መፍጠር በሚቻልባቸው ላይም መነጋገራቸው ተገልጿል።

ከዚህ በተጨማሪ ምርጫው ፍትሃዊና ተአማኒ እንዲሆን የፖለቲካ ምህዳሩን ማስፋት በሚሉት ጉዳዮች ላይ ስምምነት መድረሱንም ተናገርዋል።

ምርጫው ከተካሄደ በኋላ ሊታዩ የሚገባቸው ዋና ዋና አጀንዳዎች ተቀርጸው የቀረቡ መሆነኑንም አቶ ግርማ አብራርተዋለ።

ህገ መንግስቱን፣ የዴሞክራሲ ተቋማት ገለልተኝነትን፣ በአገረ መንግስት ግንባታ ላይ በልዩነት የሚነሱ ሀሳቦችን እንዴት ማስተናገድ ይቻላል የሚሉ ጉዳዮች ከአጀንዳዎቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የታሪክ እና ትርክት አረዳድ ሁኔታ እንዲሁም የብሔራዊ እርቅ ጉዳይ ላይ እውነትን የማፈላለግና ያለፉ ብሶቶችን ለማከም በጋራ መረዳዳት እንዲኖር መሰራት እንደሚገባም በመድረኩ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም