ለዘላቂና ፍትሃዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል…የውሃ መስኖና ኤነርጂ ሚኒስቴር

78

አዳማ ጥር 14/2013 (ኢዜአ) ዘላቂና ፍትሃዊ የውሃ ሃብት አጠቃቀምን ለማረጋገጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው የውሃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ዲኤታ ዶክተር አብርሃ አዱኛ አሳሰቡ።

የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን የ2013 ዓ.ም. የግማሽ አመት የእቅድ አፈፃፀም በአዳማ ከተማ እየገመገመ ይገኛል።

ሚኒስትር ዲኤታው በዚህ ወቅት እንዳሉት የውሃ ሃብት ደህንነትን መጠበቅና ቀጣይነት እንዲኖረ ለማስቻል ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው።

በተለይ የሀገሪቱ ኢኮኖሚና ማህበራዊ ፍላጎት እንዲሁም የህዝብ ብዛት መጨመርና በተለያዩ አካላት ከፍተኛ የውሃ ሽሚያ በመኖሩ በተፋሰሶች ላይ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል ብለዋል።

አሁን ያለውን ከፍተኛ የውሃ ፍላጎት በማመጣጠን አቅርቦቱን ከፍ በማድረግ የተቀናጀ የውሃ ሃብት አስተዳደርን ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የማድረሱን ስራ ተግባራዊ ማድረግ ይገባል ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት የወንዝ አመራር ስራን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት ለማከናወን የተሄደበት አሰራርና ዘንድሮም በሃገር አቀፍ ደረጃ ከጣና የእንቦጭ አረምን ለማስወገድ የተፋሰሶች ባለስልጣን ያከናወነው ውጤታማ ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል”ብለዋል።

የተፋሰሶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አዳነች ያሬድ በበኩላቸው እንዳስረዱት የውሃ ግኝትና ጥራት እንዲሁም መጠንን ደህንነት በማስጠበቅ ፍትሃዊ ክፍፍል ለማድረግና የተፋሰሶች ቀጣይነት ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ ቀዳሚ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በተለይም የገጸ-ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ አቅም ከማጥናት ባለፈ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን ለሚመለከቱ ጉዳዮች አስፈላጊውን ትንተና በመስጠት መንግስት ለምክክርና ድርድር ጥቅም ላይ እንዲያውል የሚረዱ ስራዎች በባለስልጣኑ እየተከናወኑ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

በዚህ ግማሽ ዓመት ተፋሰሶችን ከተለያዩ መጤ አረሞች ከመከላከል አኳያም አበረታች ስራ እየተከናወነ መሆኑን ገልጸው ለዚህ ማሳያም ጣና ሐይቅ ላይ ተንሰራፍቶ የሚገኘውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ባለስልጣኑና ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላትን በቅንጅት በማሳተፍ ከ90 በመቶ በላይ ለማስወገድ መቻሉን ተናግረዋል።

በቀጣይም በሌሎች የውሃ አካላት የተንሰራፋውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ዶክተር አዳነች ገልፀዋል።

በግምገማ መድረኩ ላይ ከ500 በላይ የሆኑ የክልሎችና የተፋሰስ ባለስልጣን አመራሮችና ሠራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም