ምርታችንን ለህብረት ስራ ማህበራት በማቅረብ በተገቢው ዋጋ እየሸጥን ነው…የጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች

142

ጎባ ጥር 14/2013 (ኢዜአ) ምርታችንን ለህብረት ስራ ማህበራት በማቅረብ በተገቢው ዋጋ እየሸጥን ነው ሲሉ በምስራቅ ባሌ ዞን የጊኒር ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ።

በዞኑ 158 መሰረታዊ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበራትና ሁለት ዩኒዬኖች አርሶ አደሩን እየደገፉ መሆናቸውን የዞኑ ህብረት ስራ ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በጊኒር ወረዳ  የአቃሻ የገበሬዎች ህብረት ስራ ማህበር አባል አርሶ አድር  ኡመር ጣህር ለኢዜአ እንደገለጹት በግብርና ስራ ተሰማርተው የተለያዩ ሰብሎችን የማምረት የቆየ ልምድ ቢኖራቸውም በገበያ እጦትና በደላሎች ተጽእኖ የልፋታቸውን ያክል ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕብረት ሥራ ማህበሩ ስር ተደራጅተው ምርታቸውን ለአገር ውስጥ የምግብ ፋብሪካዎች በማቅረብ የተሻለ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል። 

ሌላው የማህበሩ አባል አቶ ሱልጣና ሃጂ አህመድ በበኩላቸው በህብረት ሥራ ማህበራት ከመደራጀታቸው በፊት ምርታቸውን ደላሎች በሚያስቀምጡት ዋጋ ብቻ ለመሸጥ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ከአካባቢያቸው አርሶ አደሮች ጋር በመደራጀት የሕብረት ሥራ ማህበሩ  አባል መሆናቸው የነበረባቸው የገበያ ችግር ከማቃለሉ በላይ ከደላሎች ተጽዕኖ ነጻ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

"ማህበሩ  የግብርና ግብአቶችንና ምርጥ ዘሮችን በምንፈልገው ጊዜና መጠን ስለሚያቀርብልን በሄክታር የምናመርተውን ስንዴ ከ20 ወደ 65 ኩንታል ማሳደግ ችለናል" ብለዋል፡፡

የኦዳ ሮባ ገበሬዎች ሕብረት ሥራ ዩኒዬን ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ እሸቱ ዩኒዬኑ ከአስር ዓመት በፊት በስሩ ካሉ ህብረት ሰራ ማህበራት አባል ከሆኑ 512 አርሶ አደሮች በተዋጣ 115 ሺህ ብር ካፒታል የተቋቋመ መሆኑን አስታውቀዋል።

ዩኒዬኑ የዳቦና ማካሮኒ ስንዴ ፣ ቡና፣ ጤፍና ሌሎች ምርቶችን በማህበራት አማካኝነት ከአርሶ አደሩ በመረከብ ለአካባቢና ለማዕከላዊ ገበያ እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል ።

አርሶ አደሮሩ ለሚያመርታቸው ለሌሎች የሰብል ምርቶችም ገበያ እንዲያገኝ እያደረገ መሆኑን አመልከተዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ዩኒየኑ በማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር አቅርቦት እንዲሁም በትራክተርና ኮምባይነር የክራይ አገልግሎት በመስጠት አርሶ አደሩን እየደገፈ ነው።

ዩኒዬኑ የቡና መፈልፈያና የሰንዴ ምርት ማቀነባበሪያ ማሽን በአካባቢው በመትከል በምርቱ ላይ እሴት ጨምሮ ለመዕከላዊ ገበያ በማቅረብ አርሶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ አቅዶ እየሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የምስራቅ ባሌ ዞን የሕብረት ሥራ ማህበራት ማደራጃና ማስፋፊያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጥግነህ ፈዬ በበኩላቸው የሕብረት ሥራ ማህበራትና ዩኒዬኖች የአካባቢውን አርሶ አደር ተጠቃሚ እንዲያደርጉ በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዮኖች የትራክተርና ኮምባይበር ኪራይ አገልግሎት፣ የአረም መከላከያ መድኃኒትና በመሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች አቅርቦትና ሽያጭ በተመጣጣኝ ዋጋ ለአባልና ሌሎች አርሶ አደሮች እያቀረቡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በዞኑ የሚገኙ ህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዬኖች በዘንድሮ የመኽር ምርት ወቅት ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ ከባንክ በመበደር የአርሶ አደሩን ምርት በመግዛት ለመዕከላዊ ገበያ በማቅረብ የደላላን ተጽእኖ እንዲያስቀሩ  እየተሰራ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ የምስራቅ ባሌ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሰለ አለሙ ናቸው፡፡ 

በምስራቅ ባሌ ዞን 23 ሺህ አባል አርሶ አደሮችን ያቀፉ 158 የገበሬዎች ኀብረት ስራ ማህበራትና ዩኒዬኖች እንዳሉ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም