የጥምቀት በዓል የቱሪዝም ዘርፉን አነቃቅቶታል-መምሪያው

79

ጎንደር፣ ጥር 14/2013 (ኢዜአ )-በጎንደር ከተማ የተከበረው የጥምቀት በዓል የሃገር ውስጥ ጎብኝዎች ፍሰትን በመጨመር የቱሪዝም ዘርፉን ያነቃቃው መሆኑን የከተማው ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ አስታወቀ።

የቱሪዝም ዘርፉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተነቃቃ መምጣቱን አስጎብኝዎችና ባለ ሆቴሎችም ጠቁመዋል።

የመምሪያው ሃላፊ አቶ አደባባይ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንደገለጹት ጎንደር ያሏት  ጥንታዊ ቅርሶችና ባህሎች የቱሪዝም ከተማ እንድትሆን አድርገዋታል።

ከከተማዋ አጠቃላይ ኢኮኖሚ 60 በመቶ የሚሆነው የቱሪዝም ዘርፉን መሰረት ያደረገ እንደሆነ ገልፀዋል።

ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ በሰላም አጦት ካለፈው አመት ወዲህ ደግሞ የኮሮና ክስተት ተከትሎ ወደ አካባቢው የሚመጡ የሀገርና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥር እየቀነሰና የዘርፉ እንቅስቃሴ ተዳክሞ መቆየቱን አመልክተዋል ።

የአገልግሎት ሰጭ ተቋማት፣ ሆቴሎች፣ ሎጆችና በመሰል ዘርፎች የተሰማሩ አካላት ላይ የኢኮኖሚ ጫና ማሳደሩን ጠቁመዋል።

አሁን ላይ የቱሪዝም ዘርፍን ለማነቃቃት በተቀናጀ አግባብ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ሃላፊው ተናግረዋል።

ቅርሶችን መልሶ የማስተዋወቅ፣ ስብሰባዎች በከተማው እንዲካሄዱ ሁኔታዎችን የማመቻቸት፣ የጉብኝት ማህበራትን የማንቀሳቀስና ተዘግተው የቆዩ የአገልግሎት ተቋማት ወደ ስራ እንዲገቡ የማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።

እየተሰሩ ባሉት ስራዎች ለውጥ መምጣቱን የገለጹት ሀላፊው በተለይም ከገና ወዲህ የሀገር ውስጥ ጎብኝዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን አመልክተዋል።

በተለይም የጥምቀት በዓል እጀጉን ተቀዛቅዞ የቆየውን የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ እንዲነቃቃ ከፍተኛ እድል መፍጠሩን አቶ አደባባይ አብራርተዋል።

አሁን ላይ ሆቴሎች፣ ሎጆች፣ የአገልግሎት ሰጭ ቋማት፣ የባህል አልበሳት ሻጮችና ሌሎች ተቋማት ወደ ሙሉ እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸውን አስታውቀዋል።

በጎንደር ከተማ የታየ በላይ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ አብረሃም አምባቸው በበኩላቸው በአካባቢው የተፈጠሩ ተደራራቢ ችግሮች እንዲሁም የኮሮና ክስተት በሆቴል ስራው ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ተናግረዋል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተስፋ ሰጭ እንቅስቃሴዎች እየታዩ መሆኑን ጠቁመው በተለይም የጥምቀት በዓል የተሻለ እድል መፍጠሩን ገልፀዋል።

ባለፉት ጊዜያት እጅግ አስቸጋሪ የሚባሉ ጊዜያትን ማሳለፋቸውን የገለፁት ደግሞ የጉዛራ አስጎብኝዎች ማህበር አባል አቶ እያሱ አማረ ናቸው።

በቱሪዝም ዘርፉ ላይ የተከሰተው ችግር አስጎብኝዎች ሙሉ በሙሉ ከስራ ውጭ ሆነው መቆየታቸውን ጠቁመው አሁን ላይ የተሻለ ሁኔታ እየተፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን እየተስተዋሉ ያሉ መነቃቃቶችም ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መንግስት ዘርፉን የመደገፍ ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም