"ከትናንት በመማር ዛሬን መኖር"

75

በገዛኸኝ ደገፉ (ኢዜአ)

የተጠናቀቀው የፈረንጆቹ 2020 ዓመት የየዕለት ዜናና የአንዳንድ አገራት የውዝግብ ምንጭ ሆኖ የቆየው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መፍትሔ ሳይገኝለት ወደ 2021 ተሸጋግሯል። ይልቁንም ቫይረሱ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ባህሪዩን በመቀየር አዲስ ዝርያ ተፈጥሮ በፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል። ኮሮና ቫይረስ አሁንም ሀገራትን እያስጨነቀ፣ ለሁለተኛና ለሶስተኛ ጊዜ ነዋሪዎቻቸውን በቤታቸው እንዲቆዩ እያስገደደ ነው።

መነሻውን ከቻይናዋ ዉሃን ከተማ ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተበት የመጀመሪያዎቹ ቀናት ጀምሮ የህክምና ባለሙያዎችና ተመራማሪዎች የቫይረሱን ምንነት፣ ባህሪ፣ የስርጭት አቅምና ሁለንተና ለመበየን ያግዙናል ያሏቸውን ሳይንሳዊ ሞዴሎች ለማዘጋጀት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርጉም ምንነቱ ሳይታወቅ የስርጭት አድማሱን አስፋፍቶ መላውን የዓለማችን አገሮች አዳርሷል።  

የቫይረሱን ስርጭት በየእለቱ እየተከታተለ ለህዝብ ይፋ የሚያደርገው የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ በፈረንጆቹ ጥር 2021 የመጀመሪያ ሳምንት ባወጣው መረጃ መሰረት በዓለማችን በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ79 ሚሊዮን በላይ ደርሷል። በበሽታው ምክንያት ከ2 ሚሊዮን ሰዎች በላይ ህይወታቸውን አጥተዋል። በዚሁ መረጃ መሰረት በኢኮኖሚ የበለጸገችው አሜሪካ  ከ24 ሚሊዮን በላይ ዜጎቿ በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን የሟቾች ቁጥርም ከ4 መቶ ሺህ በላይ ደርሷል። በተመሳሳይ በህንድ፣ በብራዚል፣ በሩሲያ፣ በእንግሊዝና በመሳሰሉ አገራት ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ ይገኛል።

በአፍሪካ አህጉር በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ3 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ከ80 ሺህ በላይ ሆኗል። የተሻለ ኢኮኖሚ እንዳላት የሚነገርላት ደቡብ አፍሪካ ከአህጉሩ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ትገኛለች። ከደቡብ አፍሪካ ቀጥሎ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና ግብጽ እንደቅደም ተከተላቸው የተቀመጡ ሲሆን ኢትዮጵያ አምስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

በርካታ አገራት ዛሬ ላይ ዋጋ እያስከፈላቸው የሚገኘው ቀደም ሲል ለቫይረሱ ስርጭት የሰጡት የተሳሳተ ግምት ነው። የደቡብ አሜሪካዋ ብራዚል ከዓለማችን በኮሮና ቫይረስ ከተጠቁ አገሮች መካከል በ3ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ጄር ቦልሶናሮ ስለኮሮና ቫይረስ ሲናገሩ “አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አያስፈልግም፤ ቫይረሱ በራሱ ጊዜ ይጠፋል" ሲሉ ይናገሩ ነበር። ፕሬዝዳንቱ ቫይረሱን ለመከላከል ከፍተኛ ቸልተኝነት በማሳየታቸው አሁን ሕዝባቸው ዋጋ እየከፈለ ነው።

ተሰናባቹ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም ለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሰጡት ትኩረት እጅግ አነስተኛ እንደነበር እንደ ሲ ኤን ኤን በመሳሰሉ ትላልቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እስከዛሬ ይተቻሉ። ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ቫይረሱን “የቻይና ጉንፋን” በማለት ሲያጣጥሉት ነበር። በርካታ አሜሪካዉያን ኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ እንደተከሰተ መወሰድ የነበረባቸዉ እርምጃዎች በወቅቱ ቢወሰዱ ኖሮ ጉዳት ሳይደርስ የብዙ አሜሪካዉያንን ህይወት መታደግ ይቻል ነበር ብለዉ እንደሚያምኑ ሲ ኤን ኤን በአንድ ወቅት ዘግቦ ነበር። ይሁን እንጂ ትራምፕ ቫይረሱን የቻይና ጉንፋን ከማለት የዘለለ ክብደት ባለመስጠታቸዉ አሜሪካ በቫይረሱ በተያዙ ሰዎችም ሆነ በሟቹች ቁጥር ከዓለም የመጀመሪያ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እጅግ ከበረታባቸው አገራት አውሮፓዊቷ ጣሊያን ተጠቃሽ ናት። ጣሊያን በርካታ ዜጎቿን በሞት ያጣች ሲሆን በአንድ ወቅት መንግሥት የሚያደርገው ጠፍቶት ሟች መቁጠርና መቅበር የዕለት ተዕለት ተግባሩ ሆኖ ነበር። በሰሜናዊ ጣሊያን በምትገኘው የቤርጋሞ ግዛት ባሉ የህክምና ማእከላት ውስጥ በመሞትና በመኖር መካከል ያለው ግብግብ አሁንም እንደቀጠለ ነው። በቤርጋሞ ግዛት ድንገተኛ የህክምና መስጫ ክፍሎች ውስጥ ያሉ አልጋዎችና የመተንፈሻ ማሽኖች ከፍተኛ እጥረት እንዳጋጠመ ስካይ ኒውስ ያወጣው ዘገባ ያመለክታል። በዚሁ ዘገባ ላይ እንደተጠቀሰው በአንድ ሆስፒታል በህክምና የሚያገለግሉት ዶክተር ሎሬንዞ ግራዚዮሊ “ስራዬ በእጅጉ የሚያስጨንቅ ልፋትና ድካም እንዳለበት የማውቅ ቢሆንም በህይወቴ ይሄንን የመሰለ ጭንቅትና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ ገብቼ አላውቅም፤ እዚህ የሚታዩት ነገሮች ሁሉ በጣም ከባድና ከቁጥጥር ውጭ መሆናቸው ስራችንን ከምንጊዜውም በላይ አስቸጋሪ አድርጎታል” በማለት ስለ ሁኔታው አስጨናቂነት ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ቬትናም፣ ታይዋን፣ ታይላንድና የመሳሰሉ አገራት የቫይረሱ ስርጭት ሊያደርስ የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ቀውስ ቀድመው በመገመታቸው ባደረጉት ከፍተኛ ርብርብ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ፣ ጭምብል የማድረግ ግዴታዎችን በመጣል በቁርጠኝነት እንዲተገበር ማድረግ በመቻላቸው የከፋ ጉዳት አላጋጠማቸውም። በእንግሊዝ የሚታተመው ኔቸር መጽሄት እንደዘገበው በሲንጋፖር፣ በኒው ዚላንድ እና በአይስላንድ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በስፋት የመመርመርና የስርጭቱን ደረጃ የመለየት እንዲሁም የለይቶ ማቆያ እርምጃዎች ወረርሽኙን በአብዛኛው እንዲቆጣጠሩት አስችሏል።

በኢትዮጵያ ወረርሽኙ ከመከሰቱ በፊትና ከተከሰተ በኋላ ስርጭቱን ለመቀነሰ የሚያስችሉ እርምጃዎች ሲወሰዱ ቆይቷል። መንግስት ለጉዳዩ በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ፣ የትምህርት ተቋማት እንዲዘጉ በማድረግና የሃይማኖት ተቋማትም  ከዚህ በፊት እንደተለመደው በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በስፈራው እንዳይሰበሰቡ በማድረግ እንዲሁም ህብረተሰቡ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎችን እንዲጠቀም በማድረግ ወረርሽኙን ለመከላከል የተደረገው ርብርብ ከፍተኛ ነበር። ስለቫይረሱ መተላለፊያና የመከላከያ መንገዶች በተመለከተ ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው በመገናኛ ብዙሃንና በተለያየ መንገዶች መልእክቶች እንዲተላለፉ በመደረጉ እስካሁን የከፋ ጉዳት አላስከተለም። 

ይሁን እንጂ ህብረተሰቡ ከጊዜ ወደጊዜ በሚያሳየው መዘናጋትና ቸልተኝነት የተነሳ ወረርሽኙ እንደገና ማንሰራራት በመጀመሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ስጋት ደቅኗል። የጤና ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያመለክተው በአገራችን የኮቪድ-19 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገላቸው ሰዎች ብዛት ከ1 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ የደረሰ ሲሆን ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ132 ሺህ በላይ ነው። ከ2 ሺህ በላይ ዜጎች ደግሞ በቫይረሱ ምክንያት ህይወታቸውን አጥተዋል።  

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ በሰጠው መግለጫ በየቀኑ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው ለሕክምና ክትትል ወደ ሕክምና ማዕከል ከሚገቡት ታማሚዎች ውስጥ አብዛኛው ጽኑ ህሙማን ሕክምና ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን ከነዚህ ውስጥም ከ40 እስከ 45 የሚሆኑት ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሣሪያ (Mechanical Ventilator) የሚጠቀሙ ናቸው፡፡  እስካሁን ባለው ሁኔታ የጽኑ ሕክምና ክፍል ከገቡት ውስጥ 59 በመቶ ያህሉ ሕይወታቸው አልፏል፡፡ በአሁኑ ሰዓት የጽኑ ሕክምና አገልገሎት የሚፈልጉ የህሙማን ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረ በመሆኑ በተለይ በአዲስ አበባ ከጤና ተቋማት የመቀበል አቅም በላይ እየሆነ መጥቷል።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕብረተሰባችን ውስጥ እየተስተዋለ ያለው ቸልተኝነትና መዘናጋት በዚህ ከቀጠለ፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደ ሀገር ካለን ውስን የጽኑ ህሙማን እንክብካቤ አቅም በላይ ሊሆን እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት መኖሩን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። የኮሮና ወረርሽኝ በሀገር፣ በማህበረሰብ ብሎም በቤተሰብ ደረጃ እያደረሰ ያለውንና ሊያስከትል የሚችለውን የሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ስነ-ልቦናዊ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን የመከላከል ስራ ለአፍታም ቢሆን ጊዜ ሊሰጠው አይገባም። ከትናንትና በመማር ዛሬን በመኖር ለነገ ማለም ከእያንዳንዱ ይጠበቃልና።

አሁን ላይ ቫይረሱን ለመግታት ያስችላሉ የተባሉ ክትባቶች ስለመገኘታቸውና አንዳንድ በኢኮኖሚ የበለጸጉ አገራትም ዜጎቻቸውን መከተብ መጀመራቸውን በስፋት እየተነገረ ቢሆንም ቫይረሱ ባህሪውን እየቀያየረና የመተላለፍ ፍጥነቱም ከፍተኛ መሆኑን እየተዘገበ ይገኛል። እያንዳንዱ ሰው የሚያሳየው ባህሪና የሚወስደው እርምጃ ህብረተሰቡ ላይ የሚያሳድረው በጎም ሆነ አፍራሽ ተጽእኖ የጎላ በመሆኑ አሁን የሚታየው መዘናጋትና ግዴለሽነት ተጨማሪ የህይወት ዋጋ ከማስከፈሉ በፊት ከትናንት መማርን ለአፍታም ቢሆን ልንረሳው አይገባም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም