የአድዋ ድል 125ኛው በዓል በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች ይከበራል

117

አዲስ አበባ፣ ጥር 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) የአድዋ ድል 125ኛ ዓመት በአገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ገለጹ።

የበዓሉ መለያ አርማ (ሎጎ) ይፋ ሆኗል፡፡

ሚኒስትሯ በዓሉን በማስመልከት በሰጡት መግለጫ በዓሉ “አድዋ የኅብረ ብሄራዊ አንድነት ዓርማ” በሚል መሪ ቃል በመላ አገሪቱ ይከበራል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊያን ዘመናዊና ብዛት ያለው የጦር መሳሪያዎች ታጥቆ የመጣውን የጣልያን ወራሪ ጦር በአእምሮ ብስለት ተቋቁመው ድል እንዳደረጉትም አስታውሰዋል፡፡

“ድሉ ከኢትዮጵያ አልፎ የመላ የጥቁር ህዝቦች መሆኑን ለዓለም ለማስተዋወቅና መጪው ትውልድ ከአባቶቹ ጀግንነት ትምህርት ለመቅሰም ያስችላል” ብለዋል ዶክተር ሂሩት፡፡

በዓሉ በእግር ጉዞ፣ በኪናዊ ዝግጅቶችና በፓናል ውይይት ጭምር እንደሚከበር ገልፀው፤ በዓሉን በድምቀት ለማክበር በኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የሚመራ ኮሚቴ መዋቀሩንም ተናግረዋል፡፡

ከየካቲት 10 እስከ 23 ቀን 2013 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ በክልሎች በተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚከበር ሚኒስትሯ አመልክተዋል፡፡

በዘንድሮ በዓል ላይ በዓድዋ ጦርነት ጀግኖች መታሰቢያዎች እንደሚሰየሙ ተጠቁሟል፡፡

“በተለይ ወጣቱ ትውልድ በድሉ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦችን ተሳትፎ እንዲገነዘብ ይደረጋል” ብለዋል፡፡

በዓሉ የካቲት 10 በጋምቤላ ክልል ተጀምሮ፣ የካቲት 23 በትግራይ ክልል አድዋ ላይ እንደሚጠናቀቅ ተመልክቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም