የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ጥር 20 እና 21 በመቐሌ ዩኒቨርሲቲ ኹሓ ካምፓስ ተቀብሎ እንደሚያስተምር አስታወቀ

78

አዲስ አበባ፣ጥር 13/2013 (ኢዜአ) የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎችን ጥር 20 እና 21 በመቐሌ ዩኒቨርሲቲ ኹሓ ካምፓስ ተቀብሎ እንደሚያስተምር አስታወቀ።

የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ገብረእየሱስ ብርሃነ የዩኒቨርሲቲውን የመማር ማስተማር ሂደት አስመልክተው ለመገናኛ ብዙሃን ለመግለጫ ሰጥተዋል።

በትግራይ ክልል እየተወሰደ ባለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ተቋርጦ የነበረው የአክሱም ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ሂደት በመቐሌ ዩኒቨርሲቲ ኹሓ ካምፓስ ይጀመራል ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር እና መቐሌ ዩኒቨርሲቲ ጋር በተደረገ ውይይት ጥር 20 እና 21 ቀን 2013 ዓ.ም ተመራቂ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ጉዳይ ተማሪዎችም ሆኑ ወላጆች የደህንነት ስጋት ሊገባቸው አይገባም ያሉት ፕሬዚዳንቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ መገኘት አለባቸው ብለዋል።

በዘንድሮ አመት ሌሎች ተመራቂ ያልሆኑ ተማሪዎችንም ጥሪ በማድረግ የሚያስተምር መሆኑንም ገልጸዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደርና የመሰረተ ልማት ጉዳዮች ዳይሬክተር ሰለሞን አብርሃም፤ መንግስት በትግራይ ክልል በወሰደው የህግ ማስከበር እርምጃ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ዪኒቨርሲቲዎች የመማር ማስተማር ሂደት ተስተጓጉሎ እንደነበር አንስተዋል።

በዋናነት በአክሱም እና በአዲግራት ዩኒቨርሰቲ የመማር ማስተማር ሂደቱን ማስቀጠል እንዳልተቻለም አንስተዋል።

የመቐሌ እና ራያ ዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎቻቸውን ማስመረቃቸውን አስታውሰው በአክሱም እና አዲግራት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት በመቐሌ ዩኒቨርሲቲ እንዲቀጥል የማመቻቸት ስራ መስራቱን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም