በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ የንግድና መጠጥ ቤቶችን ተጽዕኖ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ

162

አዲስ አበባ፣ጥር 13/2013 (ኢዜአ) በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ የንግድና መጠጥ ቤቶችን ተጽዕኖ ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ገለጸ፡፡

ትምህርት ቢሮው "በመልካም ስብእና የታነፁ" ተማሪዎችን ለማፍራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር መክሯል፤በጋራ ለመስራትም ስምምነት ተፈራርሟል።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ አዲሱ ሻንቆ በስነ ምግባር የታነፀ ትውልድ ለመፍራት ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዚህም በትምህርት ተቋማት አካባቢ የመማር ማስተማር ሂደት የሚያውኩ የንግድ፣ መጠጥ ቤቶችና መሰል ተቋማትን ተጽዕኖ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

መልካም ስብዕና ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት የወላጆች፣ የትምህርት ተቋማት፣ መምህራንና ሌሎችም አካላት ተሳትፎና ድጋፍ ወሳኝ መሆኑንም አንስተዋል።

በትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አዋኪ ተግባራትን ለመከላከል፣ ተማሪዎችን ለአጓጉል ተግባራት እንዳይጋለጡና ብቃትና መልካም ስነ ምግባር የተላበሰ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል የጋራ የመግባቢያ ስምምነትም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ተፈራርሟል።

ቢሮው ስምምነት ከተፈራረማቸው መካከል የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ፣ ትምህርት ሚኒስቴር፣ አገር አቀፍ የፈተናዎች ኤጀንሲና የከተማ አስተዳደሩ ማህበራዊ ዘርፍ ቋሚ ኮሚቴ ይገኙበታል፡፡

የአዲስ አበባ መምህራን ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ድንቅዓለም ቶሎሳ፤ ማህበራቸው በመማር ማስተማር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማቃለል በተዘጋጀው ስምምነት የድርሻውን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየትም ወላጆች ልጆቻቸው ከትምህርት ቤት በስነ-ምግባር ታንጸው እንዲወጡ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በተጨማሪም ትምህርት ቤቶች አካባቢ የሚስተዋሉ አላስፈላጊ ነገሮችን ለማስቆም ቢሮው ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች አቅራቢያ ተማሪዎችን የሚያውኩ የንግድ ፈቃዶች መሰጠት እንደሌለባቸውም አንስተዋል።

ከሌሎች የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራትም ወሳኝ ነው ሲሉ ሃሳባቸውን ሰንዝረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም