በዞኖቹ 512 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው

59

ነገሌ/ ነቀምቴ ጥር 13 /2013(ኢዜአ)-በኦሮሚያ ክልል በጉጂና ምእራብ ወለጋ ዞኖች 512ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የየዞኖቹ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤቶች አስታወቁ። 

የጉጂ ዞን ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ታደሰ ብዙነህ ለኢዜአ እንደገለጹት ዘንድሮ 270 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራ ለማካሄድ ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።


የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራው 391 ተፋሰሶችን መሰረት በማድረግ እየተካሄደ መሆኑን ተናግረዋል።


በልማቱ 255 ሺህ 714 የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ መሆናቸውን አመልክተዋል ።

በአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል 23 ሺህ ኪሎ ሜትር የእርከን ስራና የ2 ሚሊዮን ችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል ።


በአርብቶ አደሩ አካባቢ ጉዳት የደረሰበት 12 ሺህ 656 ሄክታር ግጦሽ ሳር ከንክኪ ነጻ ለማድረግ የማካለል ስራ እንደሚካሄድም አመላክተዋል።


የዘመቻ ስራው ከተጀመረ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ አንድ ሺህ የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮና የ500 ኪሎ ሜትር እርከን ስራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

በዞኑ ሊበን ወረዳ የከላዳ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ናስር አብደላ አካባቢያቸው የእንስሳት እርባታ በስፋት የሚካሄድበት በመሆኑ በተደጋጋሚ ለግጦሽ መራቆት የተጋለጠ መሆኑን ተናግረዋል።

“ባለፈው አመት ባካሄድነው የማካለል ሰራ ተጎድተው የነበሩ የግጦሽ መሬቶች አረንጓዴ መልበስ ጀምረዋል” ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ በምዕራብ ወለጋ ዞን በ20 ወረዳዎች ውስጥ 242 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ያካለለ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የዞኑ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታውቋል ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የተፋሰስ ልማትና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራው ከጥር 4 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ 487 ተፋሰሶችን መሰረት አድርጎ እየተካሄደ ነው።


በአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራው ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል 44ሺህ 122 ኪሎ ሜትር የእርከንና የተለያዩ የእርጥበት ማቆያ ስራዎች እንደሚካሄዱ ለአብነት ጠቅሰዋል።

ጉዳት የደረሰበት 24ሺህ 785 ሄክታር መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነጻ እንዲሆን የማካለል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አመልክተዋል ።


እንደ ቡድን መሪው ገለጻ በዞኑ ለ45 ቀን በሚቆየው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 281 ሺህ 417 የህብረተሰብ ክፍሎች እየተሳተፉ ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም