የደራሼ ባህል ፌስቲቫል በጊዶሌ ከተማ እየተካሄደ ነው

77

አርባምንጭ፣ ጥር 13 ቀን 2013 (ኢዜአ) የደራሼ ህዝብ ባህላዊ እሴቶች ተጠብቀው እንዲቆዩ የሚያግዝ የባህል ፌስቲቫል በጊዶሌ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በፌስቲቫሉ በአካባቢው ባህላዊና ታሪካዊ ሀብቶች ዙሪያ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል።

የደራሼ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ አመኑ ቦጋለ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የደራሼ ብሄረሰብ ባህላዊ እሴቶች ሳይበረዙ ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማስቻል እየተሰራ ነው።

ወጣቱ ባህላዊ እሴቶቹን አውቆ እንዲጠብቅ ለማገዝ ፌስቲቫሉ መዘጋጀቱን ገልጸው፤ የአብሮነት፣ አንድነትና ትብብር ተምሳሌት የሆኑ እሴቶች የብሄረሰቡ መገለጫዎች እንደሆኑ ጠቁመዋል።

የደራሼ ብሄረሰብ ያለውን በጋራ ተረዳድቶና ተጋግዞ የመኖር ልምድ እንዲያጎለብት ፌስቲቫሉ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ባህልና ጥናት ምርምር ማዕከል የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪና የአካባቢው ተወላጅ ፍሬው ተስፋዬ በበኩላቸው “የብሄረሰቡን ባህል በተገቢው መንገድ በማጥናት ሰንዶ ማኖር ያስፈልጋል” ብለዋል።

በአካባቢው ካሉ ባህላዊ እሴቶች በተጨማሪ በርካታ ተፈጥሯዊና ታሪካዊ የመስህብ ስፍራዎች እንዳሉ ጠቁመው፤ አካባቢውን በማልማት ለጎብኚዎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የምድር ጎተራ፣ የአፈር ለምነት የሚያስጠብቅ ባህላዊ የእቀባ ግብርና ዘዴ እንዲሁም ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት ዋና የቱሪስት መስህብ እንዲሆኑ መሰራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው ፌስቲቫል በልዩ ወረዳው የሚገኙ የደራሼ፣ ኩስሜ፣ ሞስዬና ማሾሌ ብሔረሰቦች ባህላዊ እሴቶች እንደሚተዋወቁና ጉብኝትም እንደሚካሄድ ለማወቅ ተችሏል።

በፌስቲቫሉ ሥነ-ሥርዓት ከልዩ ወረዳው ሌላ ከፌደራል እና ደቡብ ክልል የተውጣጡ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ሴክተር ባለሙያዎችና ተጋባዥ እንግዶች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም