የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ የማቅረብ ግዴታቸው እንዲነሳ የውሳኔ ሀሳብ ቀረበ

86

አዲስ አበባ፣ጥር 13/2013 (ኢዜአ) ለ6ኛው አገራዊ ምርጫ የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ የማቅረብ ግዴታቸው እንዲነሳ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውሳኔ ሀሳብ አቀረበ።

ቦርዱ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ፣ የተጣበበ የምርጫ ሰሌዳና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ የድጋፍ ፊርማው እንዲነሳ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውም ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ በ2013 ዓ.ም በመላ ኢትዮጵያ ለሚያካሄደው ጠቅላላ ምርጫ፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ 1162/2011 አንቀጽ 32/2/ መሰረት የፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች የድጋፍ ፊርማ መቅረብ እንዳለባቸው ይደነግጋል።

ቦርዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ-ምግባር አዋጅ አንቀጽ 32 በጊዜያዊነት እንዲታገድ የውሳኔ ሀሳብ አቅርቧል።

ለዚህ ደግሞ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የምርጫ ወረቀት ልውውጥና ንክኪን ለመቀነስ፣ ባለው የተጣበበ የምርጫ ሰሌዳ ምክንያት ፓርቲዎቹ ፊርማ ለማሰባሰብ በቂ ጊዜ አለማግኘታቸው እንዲሁም አንቀጹ በፖለቲካ ፓርቲዎች ተደጋጋሚ ቅሬታ ያስነሳ መሆኑ በምክንያትነት አንስቷል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ በቦርዱ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ለማጽደቅ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ለዝርዝር እይታ መርቷል።

በተጨማሪም ምክር ቤቱ በዛሬው ውሎ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የቦርድ አባላትን ሹመት አስመልክቶ የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል።

እንዲሁም የህግ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌዴራል የዳኝነት አስተዳደርን እንዲሁም የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ያቀረበውን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ መርምሮ አጽድቋል።

በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የካፒታል ገበያ ረቂቅ አዋጅ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የመራ ሲሆን፤ መንግስት ከኡጋንዳ ጋር በወንጀል የሚፈለጉ ሰዎችን አሳልፎ ለመስጠትና በወንጀል ጉዳዮች የጋራ የፍትህ ትብብር ስምምነት ለማጽደቅ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ መርምሮ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መርቷል።


የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም