ያገገሙ ተፋሰሶች ለተጨማሪ የገቢ ምንጭነት እያገለገሉን ነው-አርሶ አደሮች

67

ባህርዳር፣ ጥር 13/2013( ኢዜአ)  ባለፉት ዓመታት በተከናወኑ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራዎች ያገገሙ ተፋሰሶች ለተጨማሪ የገቢ ምንጭነት እያገለገሏቸው መሆኑን በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የላይ አርማጭሆ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለጹ። 

የተፋሰስ ልማት ስራን  የህልውና ጉዳይ በማድረግ እየተሳተፉ መሆናቸውን አርሶ አደሮቹ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በወረዳው የችራ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ጎባው አስረስ እንደገለጹት ባለፉት ዓመታት በለሙ ተፋሰሶች ላይ  አፕል፣ ጌሾና የእንስሳት መኖዎችን ተክለው ተጨማሪ ገቢ እያገኙ ነው ።

ከምርት ሽያጭ በአመት እስከ 20 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።

"የተፋሰስ ልማት ስራ እስከ ልጅ ልጆቻችን የሚዘልቅ የህልውና ጉዳይ አድርገን እየተሳተፍን ነው" ያሉት አርሶ አደር ጎባው  ልማቱ የሰብል ምርታማነትና የእንሰሳት ተዋጽዖ እንዲጨምር አስተዋጻ ማድረጉን ተናግረዋል ።

"ተፋሰሱን በአግባቡ አልምተንና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ በማድረግ ጌሾና አፕል ተክለን እያለማን ነው" ያሉት ደግሞ ሌላው የቀበሌው ነዋሪ አርሶ አደር ታድሎ ዳኘው ናቸው።

በተፋሰሱ ከሚያለሙት የጌሾ ተክል ብቻ በአመት እስከ 10 ሺህ ብር ተጨማሪ ገቢ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ሁሉም አርሶ አደር የተፋሰስ ልማት ስራን ጥቅም በመረዳት በራሱ ተነሳሽነት እያከናወነ መሆኑን አመልክተዋል።

አርሶ አደር አማረ ዮሐንስ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማት ስራ የአፈር መሸርሸርን ያስቀረላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

"መሬቱ ወጣ ገባ ከመሆኑ ጋር ተያይዞም በተባበረ ሃይል በሰራናቸው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራዎች በዘላቂነት ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል" ብለዋል።

"የላይ አርማጭሆ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ንጉሴ ማለደ በበኩላቸው ወረዳውን ከሌሎች የሚለየው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ የአርሶ አደሩን ኑሮ የለወጠ በመሆኑ ነው" ብለዋል።

በወረዳው እስካሁን የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራ ከተካሄደባቸው  60 ተፋሰሶች በ31ዱ አቦካዶ፣ ማንጎ፣ ቡና፣ ጌሾ፣ አፕልና ሌሎች ፍራፍሬዎችን በማልማት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደተቻለ አመልክተዋል ።

"በተለይ ለአካባቢው የአረንጓዴ ወርቅ የሆነውን ጌሾ በስፋት ተክለው በማልማት በዓመት እስከ 300 ሺህ ብር ድረስ ገቢ የሚያገኙ አርሶ አደሮችን ማፍራት ችለናል" ብለዋል።

የክልሉ ግብርና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መለስ መኮነን በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት የተሰሩ የተፋሰስ ልማት ስራዎች የህዝቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ጀምረዋል።

"በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች የሚከናወኑ የተፋሰስ ልማት ስራዎችን በቀጣይ በስነህይወታዊ ዘዴ በማጠናከር የወጣቶችና የአርሶ አደሮችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ልንሰራ ይገባል" ብለዋል።

በክልሉ የዚህ አመት በጋ ወራት ከ4 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮችን በመሳታፍ በ8 ሺህ 300 ተፋሰሶች ላይ የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ እየተካሄደ መሆኑ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም