በአማራ ክልል ለኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ አሰራሮች ተፈትሸው ይፈታሉ- ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ

293

ጎንደር፣ ጥር 13/2013 ( ኢዜአ)-በአማራ ክልል ለኢንቨስትመንት ማነቆ የሆኑ አሰራሮችን በመፍታት በዘርፉ ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታ ይፈጠራል ሲሉ የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ አስታወቁ።

በጎንደር ከተማ በኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ ያተኮረ ባለሀብቶችን ያሳተፈ ውይይት ዛሬ ተጀምሯል።

የክልሉ ምክትል ርእሰ መስተዳደር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በወቅቱ እንዳሉት በክልሉ ባለሀብቱ ወደ ልማት ለመግባት የሚጨርሰው ሂደት ውስብስብ ነው።

አሰራሩ በርካታ ባለሀብቶችን እየተፈታተነ መሆኑን ጠቁመው “ለስራ እንቅፋት የሆኑ አሰራሮችን ፈተሾ በመፍታት ጠንካራ ኢንቨስትመንት እንዲኖር ይሰራል” ብለዋል።

የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው በከተማው በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች 500 ሄክታር የሚጠጋ መሬት መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

በከተማው አራት የኢንዱስትሪ መንደሮች መሰረተ ልማት ተሟልቶላቸው በስራ ሂደት ላይ መሆናቸውን ጠቁመው አንድ ተጨማሪ የኢንዱስትሪ መንደር ወደ ስራ ለማስገባት በሂደት ላይ መሆኑን አመልክተዋል።

ባለሀብቶችን በማበረታታትና በመደገፍ ጎንደር የቱሪዝም ኮሪደር እንድትሆን እየተሰራ መሆኑን ከንቲባው አስታውቀዋል።

በውይይቱ ከፌደራል፣ ክልል፣ ዞንና  ከተማ አሰተዳደር የተውጣጡ አመራሮች እንዲሁም  ባለሀብቶች እየተሳተፉ ነው።